የደብረ ታቦር ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከ48 ሰዓታት በኋላ ለደንበኞች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ አስታወቀ፡፡
በዘርፉ የራስ ኃይል መምሪያ የፕሮጀክት አስተዳደር አንድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተድላ ሰይፉ እንደገለጹት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታው በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በተቋሙ የራስ ኃይል ግንባታ መምሪያ ላለፉት አስራ አራት ወራት ሲከናወን ቆይቷል፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ላለፉት ሁለት ወራት የሙከራና የፍተሻ ሥራ ሲከናወን መቆየቱንም ነው የተናገሩት፡፡
በትላንትናው ዕለት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያውን ከአላማጣ ወደ ባህርዳር ከሚሄደው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ጋር የማገናኘት እንዲሁም በዛሬው ዕለት ደግሞ የትራንስፎርመር ፍተሻና የሙከራ ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ተድላ ገለፃ የማከፋፈያ ጣቢያው የፍተሻና የሙከራ ሥራ መጠናቀቁን ተከትሎ አስር ባለ 15 እና አስር ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ከ48 ስዓታት በኋላ ለደንበኞች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ይደረጋሉ፡፡
የፕሮጀክቱ በስኬት መጠናቀቅ ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማከናወን እንደሚቻል የታየበት ነው ያሉት አቶ ተድላ የማከፋፈያ ጣቢያው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆን ለደብረ ታቦርና አካባቢው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንደሚያነቃቃ አስረድተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የበቆጂ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የሙከራና ፍተሻ ሥራ በማከናወን ለህብረተሰቡ ኃይል ለመስጠት የሚያስችሉ የመጨረሻ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”