የአፍሪካ የኃይል ጉባዔ ሚሽን 300 በሚል መሪ ሀሳብ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ 300 ሚሊዮን አፍሪካውያንን የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡
ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ከዓለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከኢስላሚክ ልማት ባንክ፣ ከእሲያ የመሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ከፈረንሳይ ልማት ኤጄንሲ እና ከኦፔክ ፈንድ አጋሮች 53 ነጥብ 95 ቢሊዩን ዶላር መገኘቱን የአፍሪካ ልማት ባንክ ይፋ አድርጓል፡፡
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ እንደተናገሩት በአፍሪካ ከሚገኙ 600 ሚሊዮን ኤሌክትሪክ ኃይል ከማያገኙ ዜጎች ለግማሹ የኤሌትሪክ ኃይል ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።
ዕቅዱን ለማሳካት ከመንግስታት፣ ከንግድ ተቋማት፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ከልማት ባንኮች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ባሳለፈነው ሰኞ እና ማክሰኞ በታንዛኒያ ዳሬሠላም በተደረገው ጉባዔ ላይ 30 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተመጣጣኝ እና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2030 እንዲስፋፋ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በጉባዔው ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ ሀገራቱ አስፈላጊ የሆነ ለውጦች ላይ በመስራት 600 ሚሊዮን ሰዎችን ኤሌትሪክ አልባ ያደረገውን ችግር ለመታገል ቆርጠው እንደሚነሱ ቃል ገብተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን አሁን ካለበት 54 በመቶ ወደ 78 በመቶ ለማሳደግ እና በየዓመቱ ለ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤተሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያለመ የኢነርጂ ፖሊሲ ቀርፃ እየሰራች ትገኛለች፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”