ማከፋፈያ ጣቢያው በአካባቢዉ የነበረውን የኃይል አቅርቦት ችግር አቃሏል

ማከፋፈያ ጣቢያው በአካባቢዉ የነበረውን የኃይል አቅርቦት ችግር አቃሏል

የቱለፋ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ተንቀሳቃሸ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በቡልጋ ከተማ እና አካባቢው ለበርካታ ዓመታት ፈተና ሆኖ የቆየውን የኃይል አቀርቦት ችግር ማቃለሉን የቡልጋ ከተማ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት አስታወቀ።

የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ሸዋየ ማሞ እንደተናገሩት በቡልጋ ከተማ እና አካባቢው ከ256 በላይ ባለሃብቶች በአምራች ኢንደስተሪዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዘርፍ መሰማራታቸውንና ከእነዚህ ውስጥ ከ40 በላይ የሚሆኑት ወደ ምርት ገብተዋል፡፡ 

በቡልጋ ከተማ እና አካባቢዉ ለሚገኙና ወደ ምርት ለገቡት አምራች ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አብራርተዋል።

በ2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባው የቱለፋ ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በአካባቢው ያለውን የኃይል አቅርቦት ችግር እያቃለለ ቢመጣም ቀሪዎቹን ፋብሪካዎች ወደ ምርት ለማስገባት ከተማዉ ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት እንደሚያስፈልገው ገልፀዋል። 

ከተማ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችና ወደ ከተማዋ እየመጡ ያሉ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን አሁን ላይ ባለው የቱለፋ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ብቻ ለማስተናገድ የሚቻል አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በከተማዋ ያለውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ሥራ ቀድሞ እንዲያከናውን የጠየቁት አቶ ሸዋየ ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና ከተቋሙ ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የከተማ መስተዳደሩ ለኢንቨስትመንት ያለውን ተመራጭነት ግምት ውስጥ በማስገባት መመስረቱን የገለፁት ኃላፊው በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስተሮች በተለያዩ ዘርፎች በስፋት እየተስማሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

Scroll to Top