መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በኢነርጂ ዘርፍ ላይ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ በአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የመንግስት ዋነኛ ትኩረት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻልና ጫናዎችን ማቃለል ነው፡፡


የአሰላ የንፋስ ኃይል ፕሮጀክት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በኃይል ማመንጨት ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አቶ ሽመልስ አብራርተዋል።
አሰላ ቀደም ሲል በግብርና ምርታማነቷ በስፋት የምትታወቅ ቢሆንም አሁን ላይ ደግሞ በኃይል ማመንጨት በኩል ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከተች መሆኑን ገልፀዋል።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአካባቢው ያለውን ምርታማነት በማሳደግ ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ እገዛ ከማድረጉም ባሻገር አርሶ አደሩ ካለበት ባህላዊ አሰራር ወጥቶ ወደ ላቀ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲሸጋገር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡
የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ በአርሲና በአካባቢው ለረጅም ጊዜ የነበረውን የኃይል አቅርቦት ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታው ያላቸዉን ተስፋ ገልፀው የማመንጫ ጣቢያው ሥራ መጀመር ድህነትንና ወደኋላ ቀርነትን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱ የሆነ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የአካቢውን የኢኮኖሚ እድገት ከማፋጠኑም በላይ የማህበረሰቡ የኑሮ ሁኔታ ወደተሻለ ደረጃ ያሸጋግራል ብለዋል።
የዞኑ ህዝብ ያገኘውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ድህነት እና ኋላ ቀርነትን ለማስወገድ መረባረብ እንዳለበት አቶ ሽመልስ አሳስበዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

