
በ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ጅማ አባጅፋርን በመርታት ሶስት ነጥብ አግኝቷል።
በሐዋሳ ስቴዲየም በተከናወነው ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ አቤል ሀብታሙ እና ቢኒያም ካሳሁን ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሁለት ለአንድ ማሽነፍ ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከተከታዩ ንብ እግር ኳስ ክለብ በ10 ነጥብ ርቆ ሊጉን በ36 ነጥብ በመምራት ላይ ይገኛል።
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ኳስ መስርቶ በመጫወት እና ቶሎ ቶሎ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ በእጅጉ የተሻለ ሲሆን በአንፃሩ ጅማ አባጅፋር በመከላከልና አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ተገዶ ነበር።
በዕለቱ ጨዋታ ግሩም እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው አቤል ሀብታሙ ኮከብ ተጫዋች በመሆን የማሊያ ሽልማት ተበርክቶለታል።
በ16ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ መርሐግብር ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በመጪው ሀሙስ መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ከወልዲያ ከነማ ጋር ጨዋታውን የሚያከናውን ይሆናል።

