ኢትዮ-ኤሌክትሪክ መሪነቱን የሚያጠናክርበት ድል አስመዝግቧል

ኢትዮ-ኤሌክትሪክ መሪነቱን የሚያጠናክርበት ድል አስመዝግቧል

ትናንት በተከናወነው 20ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ጅማ አባ ቡናን ሁለት ለባዶ በመርታት ግስጋሴውን አሳምሯል።

የማሸነፊያ ጎሎቹን የአጥቂ መስመር ተጫዋቾቹ አቤል ሀብታሙ እና ልዑልሰገድ አስፋው በ11ኛው እና በ14ኛው ደቂቃ አስቆጥረዋል።

ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የጨዋታ ብልጫ ወስዶ ባጠናቀቀው በዚህ መርሐ ግብር ጅማ አባ ቡናዎች አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ከማድረጋቸው በስተቀር የጎላ እንቅስቃሴ ማሳየት አልቻሉም።

በዕለቱ አንድ ጎል ያስቆጠረው እና ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ልዑልሰገድ አስፋው ኮከብ ተጫዋች በመሆን ተመርጧል።

መርሐ ግብሩ ሊጠናቀቅ ስድስት ጨዋታዎች ብቻ በቀሩት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በ46 ነጥብ ሊጉን ሲመራ ዛሬ ተስተካካይ ጨዋታውን የሚያከናውነው ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በ35 ነጥብ ሁለተኛ ሆኖ ይከተላል።

ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በመጪው ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ከተከታዩ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ክለብ ጋር ወሳኙን ፍልሚያ የሚያከናውን ይሆናል።

Scroll to Top