የጣቢያውን የኦፕሬሽን ባለሙያዎች አቅም ለማሳደግ ይሰራል

የጣቢያውን የኦፕሬሽን ባለሙያዎች አቅም ለማሳደግ ይሰራል

በኢትዮ ኬኒያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ የኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና የባለሙያዎችን አቅም ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ።

በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተመራው የሥራ አመራር ቡድን በኮንቨርተር ጣቢያው እና የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል በሆነው የወላይታ ሶዶ ማከፋፈያ ጣቢያ የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የኮንቨርተር የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ግርማ  ስለ ጣቢያው የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራ አስመልክቶ ባደረጉት ገለፃ እስከ ኬኒያ የተዘረጋው 1 ሺ 45 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር 2 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል የማስተላለፍ አቅም ይዞ 2014 ዓ.ም ላይ ወደ ኦፕሬሽን ገብቷል።‌‎

ጣቢያው በተገነባበት የቴክኖሎጅ ዓይነት እና ለጎረቤት ሀገራት በሚያስተላልፈው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን በኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ለኬኒያና ለታንዛኒያ እስከ 300 ሜጋ ዋት ኃይል በአስተማማኝ ሁኔታ እያስተላለፈ እንደሚገኝና በቀጣዮቹ ወራት ይህን የማስተላለፍ አቅም እስከ 500 ሜጋ ዋት ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡‌‎

ጣቢያው የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣና ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግል ከመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦት፣ ባለሙያዎችን ከማብቃትና የልምድ ልውውጦችን ከማመቻቸት አንጻር ያሉ ክፍተቶች ሊፈቱ እንደሚገባም አንስተዋል።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ የተገነባውና ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው የኮንቨርተር ጣቢያ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራ በራስ አቅም መከናወኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ጊዜያት ተቋሙ እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን በማጠናከር ለሌሎች የኃይል መሠረተ ልማቶች ግንባታ የሚውል የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት የጣቢያው ሚና ወሳኘ መሆኑን ሠራተኞቹ በውል ተገንዝበው በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አብራርተዋል።

በጣቢያው ከባለሙያዎች ሥልጠና፣ ከደህንነት መጠበቂያ እና ከመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶችን የተቋሙ አመራር ፈትሾ እንደሚያስተካክል አረጋግጠዋል።

ተቋሙ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘውን ርዕይ ከግብ ለማድረስ የጣቢያው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሁሉ በትብብርና በጊዜ የለኝም መንፈስ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

Scroll to Top