የአየር ንብረት ለውጡ በኃይል አቅርቦቱ ላይ ችግር እንዳይፈጥር በትኩረት መስራት ይገባል

የአየር ንብረት ለውጡ በኃይል አቅርቦቱ ላይ ችግር እንዳይፈጥር በትኩረት መስራት ይገባል

በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ በኃይል አቅርቦቱ ላይ ችግር እንዳይፈጥር በትኩረት መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ አሳሰቡ።

በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተመራው የከፍተኛ ሥራ አመራር ቡድን በጊቤ ሦስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በመገኘት ውይይትና የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በዚህ ወቅት የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ሰሙ እንደገለጹት የኃይል ማመንጫ ጣቢያው በዓመት እስከ 6 ሺህ 500 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማመንጨት ለብሔራዊ የኃይል ቋት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ ከፍተኛውን ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።

የጣቢያውን የማመንጨት አቅም አስተማማኝነት ለማረጋገጥ የቅድመ መከላከል፣ የትንበያ እና የፍተሻና ጥገና ሥራዎች በጣቢያው ባለሙያዎች በዕቅድ ተይዘው እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡

ከመለዋወጫ እቃ አቅርቦት፣ አዳዲስ ሠራተኞችን የመግቢያ ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ ከማስገባት አንጻር በጣቢያው የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን ተናግረዋል።

በጣቢያው 253 ቋሚና 116 የኮንትራት ሠራተኞች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ሥራ የመልቀቅ ችግር መኖሩን አንስተዋል።

ከተሽከርካሪ አቅርቦት፣ ከቴሌኮም መሠረተ ልማት፣ በጨረታ ሊገኙ ያልቻሉ መለዋወጫ ዕቃዎች በቀጥታ ግዥ ከማሟላትና ከሠራተኛ ጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት በኩል አመራሩ ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በተቋሙ የጀኔሬሽን ቢዝነስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን ጣቢያው በዓመታዊ የኃይል ምርት ከሕዳሴ ቀጥሎ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን ከግምት በማስገባት አመራሩ ጣቢያውን ለማገዝ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

በጣቢያው እየተገነባ  ካለው የሠራተኞች መኖሪያ ቤት ግንባታ ጋር ተያይዞ መዘግየት የነበረ ቢሆንም የማስተካክያ ሥራ በመስራት እስከ ጥቅምት 2019 ዓ.ም ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸዋል።

ከሠራተኛ ማህበር ጋር በመሆን በጣቢያው ሠራተኞች የሚነሱ ችግሮችን የመለየት ሥራ መከናወኑንና በቀጣይም ለጥያቄዎቹ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የተቋሙ የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደመረ አሰፋ በበኩላቸው  ከተሽከርካሪ ጋር በተያያዘ ጊቤ ሦስትን ጨምሮ ለሌሎችም ጣቢያዎች ምላሽ ለመስጠት በግዢ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሠራተኛ ጥቅማ ጥቅሞችን በተመለከተ በተቋሙ ብቻ የሚወሰን ባለመሆኑ  የተቋሙንና የሠራተኛውን ጥቅም በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመመለስ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እንደሚሰራም አብራርተዋል።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው በሰጡት አቅጣጫ በክረምት ወራት በቂ ዝናብ ባለመኖሩ አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም እያጋጠመ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ በኃይል አቅርቦቱ ላይ ችግር እንዳይፈጥር የኃይል ማመንጫ ጣቢያው የውሃ አስተዳደርን ጨምሮ የኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ በተለየ ትኩረት መስራት አንዳለበት ጠቁመዋል።

የደህንነት መጠበቂያ እቃዎችን ለባለሙያዎች ማሟላት የተቋሙ ቀዳሚ የትኩረት ማዕከል በመሆኑ አመራሩ ከዚህ ጋር ተያይዞ የታዩ ክፍተቶች ካሉ የማስተካከያ ሥራዎችን እንደሚያከናውን አሳስበዋል።

ተቋሙ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ የሠራተኛው ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሠራ ስለመሆኑም አስታውቀዋል።

የጊቤ ሦስት ሁለተኛው ትልቁ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በመሆኑ የሀብት አስተዳደርን፣ የግድብ ደህንነትን እና የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማዘመን በኩል በተለየ ትኩረት ሥራዎች ሊከናወኑ እንደሚገባና ለዚህም የተቋሙ ከፍተኛ አመራር ጣቢያውን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

Scroll to Top