ውይይቱ በክልሉ የሚያጋጥሙ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና አገልግሎትን ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የክልሉን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማሻሻል የተጀመሩ የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ፤ በነባር የማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይም የኃይል አቅርቦትን ለማሻሻል እንደሚሰራ ገልጸዋል።
አክለውም ከአዲሱ የካሳ አዋጅ አተገባበርና በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ስርቆት ጋር ተያይዞ ከክልሉ መንግስት ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ተቋማቸው ለክልሉ የሚሰጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማሻሻል እየሰራ እንደሆነ እና በውይይቱ የቀረቡ ጥያቄዎችን ባጠረ ጊዜ ለመመለስ እንደሚሰሩ አረጋጥጠዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት(ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላትና ከህዝቡ የቀረቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎችን ለመመለስ ሁለቱ ተቋማትና ክልሉ በዘላቂነት በትብብር መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

የኃይል መሠረተ ልማቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።