ከአዲስ አበባ በ700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሶማሌ ክልል አይሻ ከተማ አቅራቢያ የተገነባው የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በይፋ ተመረቀ፡፡
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣የጅቡቱ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻን ጨምሮ የፌደራል መንግስትና የክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ከ257 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በ2009 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረ ሲሆን በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የ32 ተርባይኖች ተከላ፣ 30 የሠራተኛ መኖሪያ ቤቶችና የስዊች ያርድ እንዲሁም የማስተላለፊያ መስመር የግንባታ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ በ32 ተርባይን 80 ሜጋ ዋት ኃይል እያመነጨ ይገኛል።
የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ የዛሬውን ጨምሮ 120 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።
በኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ታሪክ የተቋሙ የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዩኒት በአማካሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ በአይሻ ቁጥር 2 የንፋስኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ላይ ተሳትፎ አድርጓል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”