የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል የፎቶ እና የስዕል አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በይፋ ተከፍቷል።
አውደ ርዕዩን የከፈቱት የኢፌዴሪ ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት 13 ዓመታት የተጓዘባቸውን ሂደቶች የሚያስቃኙ የተለያዩ ፎቶዎችና ስዕሎችን ተዟዙረው ተመልክተዋል።
ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ ተመስገን አውደ ርዕዩን በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የታደለች ሀገር ናት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ህዝቦቿን አስተባብራ በራሷ አቅም ማልማት የምትችል ሀገር መሆኗን ያሳየ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደ አድዋ በዓል ሁሉ ለአፍሪካውያን ወንድም እህቶቻችን ከድህነት አቅም ለመውጣት የሚደረግ ትልቅ የብልፅግና ድልን የምናስተምርበት ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል።
እንደ ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ገለፃ የግድቡን ግንባታ የማይፈልጉ ኃይሎች የተለያዩ ችግሮችን ለመፍጠር ቢሞክሩም በዲፕሎማሲው ዘርፍ በተሰሩ ሥራዎች አሸናፊ ሆነናል።
በአሁኑ ወቅት የአባይ ወንዝ ከዘፈንና ውዳሴ ተላቆ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል እያመረተ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
አውደ ርዕዩ ዛሬን ጨምሮ እስከ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ለጎብኝዎች ክፍት መደረጉም ታውቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የግድቡ ግንባታ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ እንዲሁም በተማሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም አካላት መጎበኘቱን የሚያሳዩ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።
በወቅቱም የኢትዮ-ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥም ያዘጋጀውን ቴምብር አስመርቋል።
በአውደ ርዕይው መክፈቻ የኢፌዲሪ ምክትል ጠ/ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሐይማኖት አባቶች፣ አምባሳደሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።


