የተቋሙ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚደረገው ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል

የተቋሙ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚደረገው ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል

በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚደረገውን ዘመቻና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋማዊ ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ገምግሞ  ለ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎቹን አስቀምጧል።

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ከሊል ሽፋ እንደገለፁት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመሰረተ ልማቶቹ ላይ ይፈፀም የነበረው ስርቆት ከህብረተሰቡን ጋር ተቀራርቦ በመሰራቱና የእኔነት ስሜት በመፈጠሩ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፡፡

​በበጀት ዓመቱ በ5 ሪጅኖች 91 ነጥብ 9 በመቶ የታወር የጥበቃ ሽፋን መሰጠቱ፣ የአካላዊ ደህንነት ጥበቃ ሥራዎች በዋና መሥሪያ ቤት፣ በሪጅኖች፣ በሰብስቴሽኖችና በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች መከናወኑና 104 አስተዳደራዊ ቅሬታዎች ቀርበው ምላሽ እንደተሰጠባቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

የተቋሙ የሕግ አገልግሎት መምሪያ  ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም በቀለ የተቋሙን ንብረት ለማስጠበቅ መምሪያው ከተቋማዊ ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መምሪያ ጋር በቅንጅት መስራቱን ገልጸዋል።  

የሰው ኃይል ሥራ አስፈጻሚው አቶ አታላይ አበበ በበኩላቸው የተቋማዊ ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መምሪያ  ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ መስራቱ ህብረተሰቡ ለተቋሙና ንብረቶቹ ያለው አመለካከትና  የእኔነት ስሜት እንዲፈጠር አደርጎታል ብለዋል፡፡

የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ የመሠረተ ልማት ደህንነትን አስተማማኝ ለማድረግ በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቋሙንና ንብረቱን “የእኔ ነው” የማለት የባለቤትነት ስሜት የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ​በግምገማው ማጠቃለያ ላይ አሳስበዋል።

በግምገማው ማጠቃለያ ላይ በተለያዩ ሪጅኖች ላይ የተቋማዊ የመስረተ ልማት ደህንነትና ጥበቃ ከፍተኛ መኮንኖች ላስመዘገቡት ውጠት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

Scroll to Top