የመስክ ምልከታው የፕሮጀክትና የኦፕሬሽን ሥራዎችን ተጨባጭ ለመገምገም ያስችላል

የመስክ ምልከታው የፕሮጀክትና የኦፕሬሽን ሥራዎችን ተጨባጭ ለመገምገም ያስችላል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የተመራው የከፍተኛ ሥራ አመራር ቡድን ያካሄደው የመስክ ምልከታ የፕሮጀክቶችንና የኦፕሬሽን ሥራዎችን አፈፃፀም ከሪፖርት በዘለለ በመገምገም አስፈላጊውን ድጋፍና አቅጣጫ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን በመስክ ምልከታው ላይ የተሳተፉ የተቋሙ አመራሮች ገለፁ፡፡

አመራሮቹ ለሦስት ቀናት የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል በሆኑት የአርባምንጭ ሁለተኛና ወላይታ ሶዶ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች፣ በኢትዮ-ኬኒያ ኮንቨርተር ጣቢያ እንዲሁም በጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያና በኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡

በተቋሙ የኢንጂነሪንግ እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ እንደገለፁት የመስክ ምልከታው አመራሩ በፕሮጀክትና በኦፕሬሽ ላይ የሚገኙ የኃይል መሰረተ ልማቶችን ከሪፖርት ባለፈ በተጨባጭ ያለውን የሥራ እንቅስቃሴ፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችንና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ድጋፍና ቀጣይ አቅጣጭ ለመስጠት ያስችላል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የሀገሪቱን የኃይል ፍላጎት ለመመለስ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ አዳዲስ እይታዎችን በመጨመር ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማስመዝገብና የተቋሙን ሀብት በአግባቡ ለመጠበቅ እንዲሁም የኦፕሬሽን ሥራዎችን ቅልጥፍና ለማሳደግ አመራሩ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

በተቋሙ ከፕሮጀክት አፈፃፀም ጋር ተያይዞ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ሊሻገራቸው ያልቻሉ እንቅፋቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው የመስክ ምልከታው በግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የታዩ መልካም ተሞክሮዎችን ወደ ሌሎች ፕሮጀክቶች በማሸጋገር ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት ምቹ መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

በተጨማሪም በየደረጃው ከሚገኙ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ለተነሱ ችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የመስክ ምልከታው ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ኢንጂነር ውድነህ ተናግረዋል።

በተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስ እና ኮምፕሊያንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዱጉማ ነዳ በበኩላቸው እንደ ኮይሻ የኃይል ማመንጫ ባሉ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ ትልቅ ማሳያ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በኦፕሬሽን ላይ የሚገኙ የኃይል መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅና በማዘመን እንዲሁም ፕሮጀክቶችን በጊዜና ወጭ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በመፈፀም የኃይል አቅርቦቱን ለማሻሻል የተቋሙ አመራር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመስክ ምልከታው የተነሱ ችግሮችንና የታዩ ክፍተቶችን በመፍታት እንዲሁም ጠንካራ ጎኖችን በማስፋት ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት አመራሩ በዕቅድ አካቶ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል፡፡

የተቋሙ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል ገ/ሚካኤል በበኩላቸው ሠራተኛው ባስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ በኦፕሬሽንና በፕሮጀክት ላይ በሚገኙ የኃይል መሠረተ ልማቶች ትልላቅ ውጤቶችን ለማስመዝገብ በትጋት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የመስክ ምልከታው ከሠራተኛው መብትና ጥቅም፣ ከሙያ ደህንነትና ጤንነት እንዲሁም የሥራ ዋስትና ከማረጋገጥ አኳያ የሚነሱ ችግሮችን አመራሩ በቅርበት ተረድቶ መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የሠራተኛ ማህበሩ በተቋሙ ውስጥ የኢንዱስትሪ ሠላም እንዲሰፍንና የሠራተኛው ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከሥራ አመራሩ ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳንኤል በመስክ ምልከታው ወቅት በሠራተኛው የተነሱ ችግሮች በሚመለከታቸው አካላት መፈታታቸውን እንደሚከታተልም አረጋግጠዋል፡፡

Scroll to Top