ተቋማት ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ግልፅና ተጨባጭ መልስ ሊሰጡ ይገባል

ተቋማት ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ግልፅና ተጨባጭ መልስ ሊሰጡ ይገባል

የመንግሥት ተቋማት ህብረተሰቡ በየደረጃው ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ግልፅና ተጨባጭ መልስ ሊሰጡ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ ገለፁ።

በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት ማብራሪያ እንዲሰጡ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ለህዝብ እንደራሴዎች በሰጡት ምላሽ ተቋሙ የኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሚያስቀምጠው ቀመር መሰረት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የመለየት ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ተቋሙ ተጨማሪ 14 አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና የማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታ ለማስጀመር በሒደት ላይ ነው።

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በነባር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግና የማዘመን ሥራዎችን በመስራት የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ እንደገለፁት ሁለቱን ተቋማት በጋራ ምላሽ እንዲሰጡ የተፈለገው ተቋማቱ በቅንጅት በመስራት የጋራ መልስ መስጠት ስላለባቸው ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ወደ ተመረጡበት አካባቢ ሲመለሱ በኃይል መሰረተ ልማት ጥበቃ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰር መሐመድ ገለፃ የከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ እና ማስተላለፊያ መስመሮችን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ በበኩላቸው ተቋማቱ ከህዝብ ለተነሱት ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች መሻሻል የታየበት ቢሆንም ህዝብ ከሚጠብቀው አንፃር ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ዘመናዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

በተቋማቱ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የሚበረታቱ መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ መሠረት ቋሚ ኮሚቴውም ሆነ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top