ተቋሙ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚመጥን የኃይል ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ነው

ተቋሙ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚመጥን የኃይል ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ነው

​የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሀገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ግቦችን ለመደገፍ የሚያስችል የኃይል ልማት ሥራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

​የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንዳስታወቁት የኤሌክትሪክ ኃይል የሀገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር ነው።

​ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የዕድገት ምዕራፍ ላይ የምትገኝ፣ ሰፊ የመሬት ሽፋንና ትልቅ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር በመሆኗ ምክንያት የኃይል ፍላጎቷ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ወደፊት ሊኖር የሚችለውን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ በጥናትና በዕቅድ ለመመለስ የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች ተነድፈው ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል።

​የመንግሥት ዋና የትኩረት አቅጣጫ በኢንዱስትሪው ክፍለ-ኢኮኖሚ ላይ መሆኑን ያብራሩት ኢንጂነር አሸብር ለአምራች ዘርፉ ዕድገትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ኤሌክትሪክ ወሳኝ በመሆኑ የተጀመሩት የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

​እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በኃይል ልማት ዘርፍ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍና የሚፈለገውን የዕድገት ደረጃ በፍጥነት ለማሳካት ብዙ መስራት ያስፈልጋል።

ተቋሙ በዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያፈሰሰ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ቢሆንም ከሀገሪቱ የረጅም ጊዜ የኃይል ፍላጎት አንፃር አሁንም ተጨማሪ ጥረት እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።

​በቀጣይም የሀገሪቱን የኢነርጂ አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ አማራጭ የኃይል ምንጮችን አቀናጅቶ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑም ነው የጠቆሙት።

በዚህም ከፀሐይ፣ ከንፋስ፣ ከጂኦተርማል፣ ከውሃና ከጋዝ በተጨማሪ የተጀመሩ የኑክሌር ኃይል ዝግጅቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ኢንጂነር አሸብር ተናግረዋል።

​ይህን ግዙፍ ሀገራዊ የኢነርጂ ፍላጎትና ግብ በመንግሥት በጀትና አቅም ብቻ ማሳካት አስቸጋሪ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ ካፒታል፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ወደ ዘርፉ እንዲገባ የተወሰዱ ቀዳሚ እርምጃዎች (Initiative) እና አዳዲስ አሰራሮች አጋዥ እየሆኑ መምጣታቸውንም አመላክተዋል።

​በዚህም የመንግሥትና የግል አጋርነት ማዕቀፎችን በአግባቡ በመጠቀም ባለሀብቶችን በስፋት በማሳተፍ የኃይል ልማቱን በተጠናከረ ሁኔታ ለማስቀጠል ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

Scroll to Top