ተቋሙ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሠረተ-ልማት ያለውን ተሞክሮ ለአንጎላ ባለሙያዎች አጋራ

ተቋሙ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሠረተ-ልማት ያለውን ተሞክሮ ለአንጎላ ባለሙያዎች አጋራ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (E-Mobility) ስትራቴጂያዊ ሽግግር ውስጥ እያከናወናቸው ያሉትን የኃይል አቅርቦትና የመሠረተ-ልማት ዝግጁነት ሥራዎች ከአንጎላ የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች አጋራ፡፡

በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ የኃይል ሲስተም ጥናት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙኒር ኑርሁሴን በልምድ ልውውጥ መድረኩ ላይ እንደገለጹት ተቋሙ በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ሽግግር ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።

ሽግግሩ ሀገራችን ለነዳጅ ገቢ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ፣ የበለፀገውን የታዳሽ ኃይል ሀብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም እንዲሁም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ከፍተኛ ረዳት እንደሚሆን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ፣ የኃይል ማከፋፈያ መሠረተ ልማቶችን ማቀድና ማስፋፋት፣ የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ይህንን የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ፍላጎትና ቀጣይ ዕድገትን ለመደገፍም ተቋሙ አሁን ላይ ያለውን አጠቃላይ አቅምና የወደፊት ዕቅዶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ ከፍተኛ የኃይል ሥርዓት መሐንዲስ የሆኑት አቶ ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ማብራሪያ አቅርበዋል።

ጥናቱ በሀገሪቱ በቅርቡ ይፋ የተደረገውን ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ትግበራ ስትራቴጂ (2025–2030) መሠረት ያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሀብታሙ ስትራቴጂው እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ 500 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትና በአዲስ አበባ የሚገነቡ 1 ሺህ 176 ጣቢያዎችን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 ሺህ 230 የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት የያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በዝርዝር የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል።

በልምድ ልውውጥ መድረኩ ላይ የተገኙት በአንጎላ የዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ዕድገት ኢንስቲትዩት (GGGI Angola) ተወካይ አቶ ሴሌስቲኖ ዴሎ  በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ግልጽ የሆነ ሀገራዊ ራዕይ እና የተቀናጀ የፖሊሲ አፈፃፀም ለአንጎላ ልዑክ መሠረታዊ ልምዶችን የመቅሰም ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር የተያዘው የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ስትራቴጂ ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ እስከ ታችኛው የመንግስት መዋቅርና በተለያዩ ሴክተሮች መካከል በሚገባ በማቀናጀት በተግባር እየተተረጎመ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያቀረባቸው የማስተላለፊያ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና የወደፊት የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች መረጃዎች ተቋሙ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለመወጣት እያደረገ ያለውን ዝግጁነት የሚያሳይ መሆኑን ያወሱት አቶ ሎ ሀገራቸው አንጎላ ይህንን ስትራቴጂያዊ አሠራርና የመሠረተ-ልማት ትስስር እንደ መልካም ተሞክሮ የምትወስደው መሆኑን ተናግረዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top