ተቋሙ በራስ አቅም የሚያከነውናቸውን የፕሮጀክት ግንባታዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ

ተቋሙ በራስ አቅም የሚያከነውናቸውን የፕሮጀክት ግንባታዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በራስ አቅም የሚያከናውናቸውን የኃይል ማከፋፈያና ማስተላለፊያ መስመር ግንባታዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል በተቋሙ የኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ፡፡

የዘርፉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ እንደተናገሩት ፕሮጀክቶችን ከዲዛይን እስከ ግንባታ ያለውን ሙሉ ሂደት በራስ አቅም በማከናወን ረገድ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አበረታች ነው፡፡

ተቋሙ ወደፊት በራስ አቅም የሚከናወኑ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የውስጥ አሰራርን ከማሻሻልና የውጭ ተፅዕኖዎችን ከመቆጣጠር አንፃር የተለያዩ የሪፎርም አቅጣጫዎችን ለይቶ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የውስጥ አሰራርን ለማሻሻል በግንባታ እና በድጋፍ ሰጪ የሥራ ክፍሎች መካከል ያለውን ቅንጅት፣ ቅልጥፍና እና የጋራ ግንዛቤ በማሳደግ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ኢንጂነር ውድነህ አብራርተዋል፡፡

የዕቃ አቅራቢዎች ተፅዕኖን፣ የገበያ የዋጋ ግሽበትን፣ የሎጂስቲክስና የፀጥታ ችግሮችን ለመቋቋም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ አብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል፡፡

በተለይም የዕቃ አቅርቦት መቆራረጥና መዘግየትን በዘላቂነት ለመፍታት ተቋሙ ወደፊት በቀጥታ ከአምራች ድርጅቶች ጋር በመገናኘት ግዢዎችን የሚያከናውንበትን የሥራ ሂደት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

በራስ አቅም የሚከናወኑ ግንባታዎችን ጥራትና ፍጥነት ይበልጥ ለማሳደግ የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።

በቀጣይም የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ባበረከቱት የሥራ ድርሻ ልክ የሚሸለሙበትንና ማበረታቻ የሚያገኙበትን የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

Scroll to Top