በአድዋ ማከፋፊያ ጣቢያ የኃይል መቆራረጥን ለማስወገድ የሚያስችል የአራት ብሬከሮች ቅየራ መከናወኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ሪጅን የአድዋ ማከፋፊያ ጣቢያ ኃላፊ ገለጹ።
ኃላፊው አቶ አብርሃ ይስሃቅ እንደገለጹት በአድዋ ማከፋፊያ ጣቢያ የነበሩት አራት ብሬከሮች በተለያዩ ምክንያቶች ብልሽት ሲገጥማቸው ቆይቷል።
በብሬከሮቹ ብልሽት ምክንያትም የማከፋፊያ ጣቢያው በሚሸፍነው የትግራይ ማዕከላዊ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የኃይል መቆራረጥ ሲያጋጥም መቆየቱን ገልጸዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በሰሜን ሪጅን የጥገናና የኦፕሬሽን መምሪያ አቅም አንድ ገቢና ሦስት ወጪ ብሬከሮች ተቀይረው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ አብርሃ ገለጻ የብሬከሩ መቀየር የማከፋፊያ ጣቢያው በሚሸፍነው የትግራይ ማዕከላዊ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ሲያጋጥም የነበረውን የኃይል መቆራረጥ በመቅረፍ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል።
የሰሜን ሪጅን የማከፋፊያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን እና ጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ክፍሌ ተስፋዬ የአራቱ ብሬከሮች ቅየራ ሥራ ሙሉ በሙሉ በሪጅኑ ባለሙያዎች መከናወኑን ተናግረዋል።
የብሬከር ቅየራው ላይ የተሳተፉ ሠራተኞች ሙያዊ አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት አጋጣሚ መፍጠሩን አብራርተዋል።
በ1989 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአድዋ ማከፋፊያ ጣቢያ 64 ሜጋ ዋት ኃይል የመሸከም አቅም አለው።


