
በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በማስፋት የአረንጓዴ ኢነርጂ ፖሊሲ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ የተቋሙ አመራር ቁርጠኛ መሆን እንደሚኖርበት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚደንት ገለጹ፡፡
ፕሬዚደንቱ አቶ ዛዲግ አብርሃ የኃይል ማመንጨት ዕድገት ትናንት፣ ዛሬ እና የወደ ፊት መጻኢ ተስፋን አስመልክተው ለተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በገለጻቸውም ዓለም ከቅድመ ኢንዱስትሪ ማህበረሰብ ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ጂኦ ፖለቲካዊ ዕድገቶች በኢነርጂ ሽግግር ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
እንደ ቻይና፣ ጀርመንና አሜሪካ ያሉ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት የነበራቸውን የነዳጅ፣ የኒውክለርና ሌሎች የኃይል ምንጮችን ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጮች በማሸጋገር ከካርቦን ልቀት የጸዳ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የፓሊሲ ለውጥ እያደረጉ መሆኑን አስታውሰዋል።
ጀርመን በ2050 ስልሳ በመቶ የኃይል ምንጯን ከታዳሽ ኃይል ለማግኘት የፖሊሲ ለውጥ ማድረጓን ለአብነት የጠቀሱት አቶ ዛዲግ ኢትዮጵያም የኢነርጂ ፖሊሲዋን በመፈተሽ ታዳሽ ኃይል ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባት ገልጸዋል።
እንደ አቶ ዛዲግ ገለጻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢነርጂ ሴክተሩን በበላይነት የሚመራ ተቋም በመሆኑ በግሎባል ኢነርጂ ሽግግር ላይ አመራሩ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርበታል።
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጯን በማስፋት በቀጠናው ብሎም በዓለም የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ፉክክር ላይ ተወዳዳሪ ሆና እንድትቀጥል በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አመራር እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
በተቋሙ ጠንካራ የኢነርጂ ፖሊሲን በመቅረጽ ፍትሐዊ የኢነርጂ ክፍፍልን ማስፈን፣ የኃይል ብክነትን መቀነስ እና የማጠራቀም አቅምን ማሳደግ እንዲሁም ወጪ ቆጣቢ የኃይል አጠቃቀም ሥርዓትን ማሻሻል የአመራሩ ቁልፍ ተግባር መሆን አለበት ብለዋል።
ስለሆነም በተቋሙ የኢነርጂ ፖሊሲ ውስጥ ብሔራዊ የተቀናጀ የኃይል ዕቅድን እና የኃይል ሽግግር ምክር ቤትን እንዲሁም የታሪፍ እና የድጎማ ሪፎርሞችን በማካተት ዘላቂና የማይበገር የአረንጓዴ ኢነርጂ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

