የሱሉልታ ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ የኢትዮጵያ ሰሜናዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ሲስተምን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን የጣቢያው ኃላፊ ተናገሩ።
ኃላፊው አቶ ዳንኤል አደኔ እንደገለፁት ጣቢያው ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ከበለስ የኃይል ማመንጫዎች የሚመረተውን ኃይል በመቀበል ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በማስተላለፍ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።


ማከፋፈያ ጣቢያው የሚጠቀማቸው ሪአክተሮች የቮልቴጅ መዛባት በሚያጋጥምበት ወቅት የግሪድ ሲስተሙን ከድንገተኛ የኃይል መቋረጥ ለመጠበቅ እና የተረጋጋ ኃይል ለማቅረብ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ጣቢያው ኃላፊ ገለጻ ጣቢያው ባለ 400፣ 230፣ 132 እና 33 ኪሎ ቮልት አቅም ያላቸው የተለያዩ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡
እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማመጣጠን እና ከህዳሴ የሚመጣውን ተጨማሪ ኃይል አስተማማኝ በሆነ መንገድ ወደ ሲስተሙ ለማስገባት ተጨማሪ የትራንስፎርመር ተከላ ለማከናወን መታቀዱን አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል።

