የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ካሉት ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ግንባታው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አቅራቢያ ላይ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ በደብረማርቆስ መስመር በ730 ኪሎ ሜትር እንዲሁም እና በአሶሳ በኩል በ830 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ 5,150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፥ በአፍሪካ ካሉ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል በግዙፍነቱ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ፕሮጀክቱ አስቀድመው ኃይል ማመንጨት በጀመሩት ሁለት ዩኒቶች 750 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ፈጥሯል፡፡ ከፕሮጀክቱ የሚመነጨው ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል በመግባት በሀገሪቷ የኢነርጂና በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
ፕረጀክቱ ኤሌትሪክ ለማመንጨት ብቻ የሚውል ሲሆን ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ፕሮጀክቱ የሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እና ትብብርን በማጎልበት ኢትዮጵያ የቀጣናዊ የኃይል ትስስር ማዕከል እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ የግድቡ ግንባታ 1,780 ሜትር ርዝመት ያለው እና 145 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ ፕሮጀክቱ በዓመት በአማካይ 15,760 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል የማምረት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እየተገነባ ነው።