በኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከዕውቀት ሽግግርና አቅም ግንባታ፣ ምቹ የሥራ ከባቢን ከመፍጠር እንዲሁም ከፕሮጀክትና ከኮንትራት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የታዩ ምርጥ ተሞክሮዎችን በአግባቡ ቀምሮ በቀጣይ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች መተግበር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።
በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተመራው የሥራ አመራር ቡድን በኮይሻ ፕሮጀክት የመስክ ምልከታ አድርጓል።


የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መብራቱ ተሾመ ለልዑኩ ባደረጉት ገለፃ ፕሮጀክቱን እስከ ግንቦት 2021 ዓ.ም ድረስ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ የዋናው ግድብ፣ የኃይል ማመንጫ ቤት፣ የውሃ ማስተንፈሻና ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በፕሮጀክቱ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ደሳለኝ በበኩላቸው ተቋሙ መሰል ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን ከመጀመሩ አስቀድሞ ዝርዝር የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት እንደሚያካሂድ ተናግረዋል።

በዚህ ጥናት ላይ ተመስርቶ በተዘጋጀው የአካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች ሥራ አመራር ዕቅድ መሰረት እስከ አሁን የሥራ ተቋራጩን አስተባብሮ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉና በፕሮጀክቱ ላይ የእኔነት ስሜትን የሚፈጥሩ ከ1 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን ማከናወኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪ ተቋሙ በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሚገኙ ሁለት ከተማ መስተዳደሮችንና ሦስት የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ኃላፊዎቹ ከወላይታ ሶዶ እስከ ኮይሻ በተዘረጋው ባለ 400 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ላይ የሚፈጸመው የብረት ምሰሶ ስርቆት፣ የፕሮጀክቱ ሰው ሰራሽ ሀይቅ የሚያርፍበት ደን ምንጣሮና ሌሎች በተቋሙ ከፍተኛ አመራር በኩል ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችንም አቅርበዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ ተቋሙ እንደሀገር የኃይል አስተማማኝነትንና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ከአጠቃላይ በጀቱ እስከ 80 በመቶው የሚሆነውን ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንደሚያውል ተናግረዋል።


በፕሮጀክቱ ከኮንትራት አስተዳደር፣ ከፕሮጀክት አመራር፣ ከዕውቀት ሽግግርና አቅም ግንባታ እንዲሁም ከምቹ የሥራ ከባቢና ከካሳ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በሌሎች ፕሮጀክቶች የነበሩ ክፍተቶች የታረሙበትና ለቀጣይ ሥራዎች ምርጥ ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ ለፕሮጀክቱ ልዩ ትኩረት በመስጠት በራሱ ፋይናንስ ግንባታውን እያከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጅነር አሸብር ፕሮጀክቱ ከነበረበት አስቸጋሪ የግንባታ ሂደት ወጥቶ ባለፉት ዓመታት ያሳየው አፈጻጸም ኮይሻ ለሌሎች ፕሮጀክቶች ሞዴል እንዲሆን እንዳስቻለው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቱ ሰው ሰራሽ ሀይቅ የሚያርፍበት ደን ምንጣሮ ሥራን በተመለከተ የሕዳሴን ልምድ በመውሰድና ዩኒቨርሲቲዎችን በማሳተፍ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በፕሮጀክቱ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመርና በማስፋት በተቋሙ የተጀመሩ ትልልልቅ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።


