ፕሮጀክቱን ዘንድሮ ከ90 በመቶ በላይ ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡

Published by corporate communication on

የባህርዳር – ወልዲያ – ኮምቦልቻ ባለ 400/230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታን በተያዘው በጀት ዓመት ከ90 በመቶ በላይ ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡

በፕሮጀክቱ እንደሚተከሉ ከሚጠበቁት 829 ምሰሶዎች ውስጥ በአሁኑ ሰዓት 746 ምሰሶ ለመትከል የሚያስችል የመሰረት ቁፋሮ ተጠናቋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ደግሞ 115 ምሰሶዎች ተከላ የተከናወነ ሲሆን ቀሪ ምሰሶዎችን የመትከል እና ገመድ የመዘርጋት ሥራዎችንም በ2013 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡

ለፕሮጀክቱ መስመር ዝርጋታ የሚሆኑ አብዛኛዎቹ የምሰሶ መትከያ ብረቶችና ገመዶች የፕሮጀክቱ ዕቃ ግምጃ ቤት ገብተዋል፡፡

ይሁንና ለ 83 ምሰሶዎች የመሰረት ቁፋሮ ለማከናወን ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች በማጋጠማቸው ቁፋሮውን ማከናወን አልተቻለም፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታውን የቻይናው ሻንጋይ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን በማከናወን ላይ ሲሆን የማስተላለፊያ መስመሩ ግንባታ ደግሞ የህንዱ ታታ ፕሮጀክትስ ሊሚትድ (TATA PROJECTS LTD) እያከናወነው ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱን በማማከር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኢነጂነሪንግ ቢሮ ነው፡፡

ለማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ 83 ነጥብ 09 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እና 337 ነጥብ 97 ሚሊየን ብር እንዲሁም ለኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ 97 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እና 886 ነጥብ 17 ሚሊየን ብር ተመድቦለታል፡፡

የባህርዳር – ወልዲያ – ኮምቦልቻ ባለ 400/230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት አጠቃላይ አፈፃፀሙ ደግሞ 48 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ እስከ 1 ሺህ ሜጋ ዋት ድረስ የማስተላለፍ አቅም አለው፡፡

ፕሮጀክቱ እስካሁን ባለው የግንባታ ሂደት ከፋይናንስ አቅርቦት በተጨማሪ የኮንትራት ማሻሻያ፣ የወሰን ማስከበር ችግርና ወደ ሃገር ውስጥ በሚገቡ የኃይል ማስተላለፊያ ዕቃዎች ላይ እስከ 35 በመቶ የሚደርስ ታክስ እንዲጣል የሚያደርግ መመሪያ መውጣቱና የኮቪድ-19 ስርጭት በታቀደው መሰረት እንዳይከናወን አድርጎታል፡፡

የባህርዳር – ወልዲያ – ኮምቦልቻ ባለ 400/230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከባህርዳር ተነስቶ የደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖችን የሚያካልል ሲሆን በየጊዜው ከወሰን ማስከበር ጋር የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው የዞን እና የወረዳ አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡

በመሆኑም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ችግሮቹን በመፍታት ለግንባታው መፋጠን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

6 + sixteen =