ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

የሠመራ አፍዴራ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ፕሮጀክትን የሲቪል እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችን ግንባታ በማጠናቀቅ የሙከራና ፍተሻ ሥራ ለመስራት መታቀዱን የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ አስታወቀ፡፡
የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጁ አቶ ኢዮሲያስ ኃይለማርያም እንደተናገሩት በፕሮጀክቱ የማከፋፈያ ጣቢያ የትራንስፎርመር ማስቀመጫ ቤት፣ የኃይል መቆጣጠሪያ ክፍል፣ የመኖሪያ እና የቢሮ ግንባታዎች በመከናወን ላይ ነው፡፡
የግንባታ ስራው ህዳር 2011 ፕሮጀክቱ ለአፍዴራ እና አካባቢው ነዋሪዎች ብሎም ለጨው ማምረቻና የአዮዲን ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ አልሞ የተገነባ ነው፡፡
በአፍዴራ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክት 40 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለው አንድ የኃይል ትራንስፎርመር እንደሚገጠምለት ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በረሃማ በሆነ አካባቢ የሚገኝ ቢሆንም ተቋራጩ ጥልቅ ቁፋሮ በማካሔድ ለግንባታ እና ለመጠጥ የሚያገለግል ውሃ ማቅረቡንና ይህም ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ለጣቢያው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሠመራ አፍዴራ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ፕሮጀክት አካል የሆነውና 195 ኪ.ሜ የሚረዝመው የሠመራ-አፍዴራ ባለ 230 ኪ.ቮ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታም በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በፕሮጀክቱ ሊተከሉ ከታቀዱት 466 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች መካከል 426 ምሰሶዎችን ለመትከል የመሠረት አርማታ መሙላት ስራ መጠናቀቁንና ከዚህ ውስጥ የ250 ምሰሶዎች ተከላ መጠናቀቁን አቶ ኢዮስያስ ገልፀዋል፡፡
የቀሪዎቹ 216 ምሰሶዎች ተከላና የኤሌክትሪክ ገመድ ዝርጋታም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ለኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክቱ ሰባት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እና 44 ሚሊዮን ብር ገደማ የተበጀተለት ሲሆን ለኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታው ደግሞ 13 ሚሊዮን ዶላር እና ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦለታል፡፡
የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን በመገንባት ላይ የሚገኘው የህንዱ ካልፓታሮ ሲሆን ናንጂንግ ዳጂ የተሰኘው የቻይና ኩባንያ ደግሞ የኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክቱን ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የጀርመኑ ትራክት ቤል ኩባንያ ደግሞ የማማከር ሥራውን በማከናወን ላይ ነው፡፡
በኃይል ማከፋፈያ እና ማስተላለፊያ ፕሮጀክቱ ላይ ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ 780 ኪ.ሜ ርቀት፤ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዞን 3 እየተገነባ የሚገኘው የሠመራ-አፍዴራ ባለ 230 ኪ.ቮ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ማህበረሠብና በአቅራቢያው ለሚገኙ ፋብሪካዎች አስተማማኝ ኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
0 Comments