ጣቢያው የምርምርና ልማት ማዕከል በማቋቋም ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል

Published by corporate communication on

የጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የምርምርና ልማት ማዕከል በማቋቋም የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

የጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ንጉሴ ማሙሻ እንደገለፁት ጣቢያው በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለይቶ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል የምርምርና ልማት ማዕከል አቋቁሟል፡፡

ጣቢያው ግዙፍ እንደመሆኑ መጠን ውስብስብ የሆኑ የአሰራር ሥርዓቶችን ለማሻሻል ጥናትና ምርምሮችን ማከናወን መጀመሩን አቶ ንጉሴ ተናግረዋል፡፡

የማዕከሉ መቋቋም በራስ አቅም የሚሰሩ ስራዎችን ለማጠናከር፣ የሠራተኞችን አቅም ለማሳደግ እና ወጪ ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

የጥገና ሥራዎች በጥናት ታግዘው መከናወናቸው የጣቢያውን የማመንጨት አቅም ከፍ እንደሚያደርግ የጠቀሱት ኃላፊው ማዕከሉ ከተቋቋመ በኋላ የተሠሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ማዕከሉ የሠው ኃይል ልማት ሥራዎችን በማከናወን ብክነቶችን ከመቀነስ ባለፈ ጊዜ ይወስዱ የነበሩ ተግባራትን አሳጥሮ በመስራት ረገድ መሻሻሎችን አስገኝቷል ብለዋል፡፡

የጣቢያው ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ሰሙ በበኩላቸው ማዕከሉ በጣቢያው የኃይል ማመንጫ፣ የጥገና እና የአስተዳደር ክፍሎች ተናበው ዕቅዶቻቸውን እንዲያሳኩ በማድረግ መፍትሔ ሰጪ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን በተሰራው ሥራም በጣቢያው የሚገኙ የሥራ ክፍሎች የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት እንዲዘምን መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በምርምርና ልማት ማዕከሉ ውስጥ ሥራ እየሠሩ የሚገኙት አቶ አማኑኤል ዳንኤል በበኩላቸው የማዕከሉ መቋቋም ዋና ዓላማ የኃይል ማመንጫ ጣቢያው በጥናታዊ ምርምሮች እንዲታገዝ በማድረግ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ሥርዓት እንዲኖረው ማስቻል ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራዎች ለመስራት እየተዘጋጀ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

አቶ አማኑኤል እንደገለፁት ማዕከሉ የምርምርና ልማት ሥራዎችን ለማከናወን የሚያግዘውን ድረ-ገፅ በመስራት የተለያዩ ፕሮጀክቶች መተግበር ጀምሯል፡፡

በጣቢያው በተደጋጋሚ ብልሽት እያጋጠማቸው ያሉ ዕቃዎችን በመለየት ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ የአጭርና የረጅም ጊዜ የምርምርና ልማት ዕቅዶችን ነድፈው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን አቶ አማኑኤል ገልፀዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

thirteen + 3 =