ጣቢያው አገልግሎቱን በብቃት፣ በጥራትና በተገቢው መንገድ እየሠጠ ነው

የማስፋፈያ እና የአቅም ማሳደግ ሥራዎች የተሠሩለት የመቱ ባለ 230/66/33/15 ኪ.ቮ. ማከፋፈያ ጣቢያ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የማከፋፈያ ጣቢያው ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጎሳ ገለጹ፡፡
አቶ ሰለሞን እንደገለፁት በ1984 ዓ.ም. ከሶር ኃይል ማመንጫ በ66 ኪ.ቮ. መስመር ኃይል በመቀበል ለመቱ እና ለአካባቢው በ15 ኪ.ቮ. ኃይል በመስጠት በይፋ ሥራ የጀመረው ማከፋፈያ ጣቢያው እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ይሁንና በ2002 ዓ.ም. ማከፋፈያ ጣቢያው በተደረገለት የማስፋፈያና የአቅም ማሣደግ ሥራ ኃይል የመቀበል አቅሙን ወደ 232 ኪ.ቮ ለማድረስ መቻሉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ከአቅም ማሳደግ ሥራው በኋላ ማከፋፈያ ጣቢያው አምስት ባለ 15 ኪ.ቮ እና ሦስት ባለ 33 ኪ.ቮ. ወጪ መስመሮች እንዲኖረው መደረጉን አንስተዋል፡፡
ከበደሌ ማከፋፈያ ጣቢያ በጥንድ ባለ 230 ኪ.ቮ መስመር የሚቀበለውን ኃይል ባሉት አምስት ባለ 15 ኪ.ቮ. እና ሁለት ባለ 33 ኪ.ቮ. ወጪ መስመሮች በኢሉባቡር ዞን የሚገኙትን 13 ወረዳዎችና ከተሞች እንዲሁም አንዱን ባለ 33 ኪ.ቮ ደግሞ በደቡብ ክልል ለሚገኘው የማሻ ወረዳ ኃይል ለመስጠት ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
ጣቢያው በ2008 ዓ.ም. በተደረገለት ተጨማሪ የማስፋፈያ ሥራ በጥንድ ባለ 230 ኪ.ቮ ወጪ መስመር ለጋምቤላ ክልል ኃይል እየሰጠ ይገኛል ፡፡
ከአዲስ አበባ በ525 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን በመቱ ከተማ የሚገኘው የመቱ ባለ 230/66/33/15 ኪ.ቮ. ከፍተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎቱን በብቃት፣ በጥራትና በተገቢው መንገድ እየሠጠ ይገኛል፡፡
0 Comments