ጣቢያው ተጨማሪ 60 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት ያስቻለ ጥገና አድርጓል

Published by corporate communication on

የጊቤ 2ኛ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያ ካሉት አራት ዩኒቶች መካከል በአንደኛው ዩኒት ላይ ሙሉ ጥገና በማድረግ 105 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ እንዲያመነጭ መድረጉን የጣቢያ የኦፕሬሽን ክፍል አስታወቀ፡፡

በጣቢያው የኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ሽመልስ አዱኛ እንደገለፁት የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ዩኒቶች እንደመጫን አቅማቸው ውሀን ለመመጠን በሚያገለግለው የመርፌ ቅርፅ ያለው የፓወር ኖዝል መቆጣጠሪያ (needle valve) ላይ ብልሽት በማጋጠሙ ምክንያት አንዱ ዩኒት ሙሉ በሙሉ ኃይል ማመንጨት አቁሞ ነበር፡፡

ይሁንና ዩኒቱን በራስ አቅም በመጠገን 105 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ አመንጭቶ ወደ ሲስተም ማስገባት ተችሏል፡፡

ቀደም ሲል እስከ 45 ሜጋ ዋት ያመነጭ የነበረው ይኸው ዩኒት ባጋጠመው ችግር ምክንያት ማመንጨት አቁሞ የነበረ ሲሆን በተደረገለት ጥገና እና የማመንጨት አቅም የማሳደግ ሥራ ተጨማሪ 60 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ እንደያመነጭ መደረጉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በዩኒት አንድ ላይ የተሰራውን ዓይነት ተመሳሳይ የጥገናና የማመንጨት አቅም የማሳደግ ሥራ በሦስተኛው ክፍል (ዩኒት 3) ላይ ለማከናወን ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሺመልስ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ወደ ተርባይን የሚገባውን ውሃ በሚቆጣጠሩ የዘይት ፍሰት መቆጣጠሪያ ሲሊንደሮች (MIV servomor piston cylinder) አጋጥሞ የነበረውን የዘይት መፍሰስ ችግር በመጠገን መቆጣጠሪያው (MIV) በጥሩ ሁኔታ እንዲሰራ መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የመቆጣጠሪያ፣የሬክቲፋየር፣ የሰርቨር ክፍል፣ ስዊች ያርድ እና የተበላሹ የማቀዝቀዣ መሳሪያዎችን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

የጥገና ሥራውን ለማከናወን የመለዋወጫ እቃ ብቻ ከውጭ መግዛት መቻሉንና  ሌሎች  ሥራዎች ግን በጣቢያው ሠራተኞችና ከማዕከል በተውጣጡ ከፍተኛ ባለሞያዎች በጥምረት የተከናወነ መሆኑን  አቶ ሺመልስ  አብራርተዋል፡፡

ይህም የሠራተኛውን ተነሳሺነትና አቅም በማሳደግ ጥሩ ልምድ የተገኘበት ነበር ያሉት ኃላፊው ከተገኘው ልምድ በተጨማሪ ጥገናውን በውጭ ለማከናወን ሲባል ይወጣ የነበረን በሚሊዮን የሚገመት ብር ማስቀረት ተችሏል ብለዋል፡፡

የጊቤ ሁለት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሀብታሙ ገረመው ጣቢያው በጥገና ሥራው ወቅት ለሚጠይቀው ማንኛውም የዕቃ እና ተያያዥ አቅርቦቶች የተቋሙ ማኔጅመንት ለሰጠው ፈጣን ምላሽና አዎንታዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

four × 1 =