ጠንካራ ተቋማዊ ባህል መኖር ለአንድ ተቋም ውጤታማነት አስፈላጊ ነው ተባለ

Published by corporate communication on

በአንድ ተቋም ውስጥ ጠንካራ ተቋማዊ ባህል መኖሩ ለተቋሙ ውጤታማነት አስፈላጊ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋም ትራንስፎርሜሽናል ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው በተቋማዊ ባህል ዙሪያ ባካሄደው ረቂቅ የዳሰሳ ጥናት ላይ ከተቋሙ የስራ ክፍሎች ከተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር ተወያይቷል።

የቢሮው ስራ አስኪያጅ አቶ አንዱአለም ኪዳኔ እንደተናገሩት በአንድ ተቋም ውስጥ ጠንካራና ግልጽ የሆነ ተቋማዊ ባህል መኖር ተቋሙ የተጣለበትን ዓላማና ግብ ለማማሳካት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

ዳሰሳ ጥናቱ ተቋሙ አሁን ያለውን ተቋማዊ ባህል ለማወቅ፣ ያለውን ክፍተት ለማሻሻልና ጥንካሬውን ለማጎልበት የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለማመላከት እንደሚያግዝም አቶ አንዱአለም ገልፀዋል፡፡

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ የዳሰሳ ጥናቱ ተቋማዊ ባህል ለተቋም ውጤታማነት ያለውን አስተዋጽኦ ለማስቀመጥ እና የኮርፖሬት ቢዝነስ ባህል ያለው ተቋም ለመገንባት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

 አውደ ጥናቱ  የተካሄደው በዳሰሳ ጥናቱ የተገኙ ግኝቶችን ከሁሉም የሥራ ክፍሎች ለተውጣጡ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ለማስተዋወቅ እና ከተሳታፊዎች ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ታስቦ እንደሆነ አቶ አንዱአለም አስታውቀዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ እንደተገለጸው ሠራተኛው ተቋሙን የራሱ አድርጎ በኃላፊነት ያለመንቀሳቀስ፣ ግብ ተኮር ባህል አለመኖር፣ ግለሰቦችና ቡድኖች ግብን ለማሳካት ግልጽ የሆነ እቅድ አለመኖር፣ ግለሰቦችና ቡድኖች በሰሩት ሥራ የእውቅናና ሽልማት ሥርዓት አለመኖር፣ የተጠያቂነት ሥርዓት ያለመዘርጋት እና የቡድን ስራ የተዳከመ መሆን የሚሉት በረቂቅ ዳሰሳ ጥናቱ የተለዩ ግኝቶች ናቸው፡፡

ከእነዚህ ግኝቶች በተጨማሪም የሥራ መሪዎች የተቋሙን እቅድ ለማሳካት በቡድን ተባብረው ያለመስራት፣ ሰራተኞች የተቋሙን እሴቶች፣ ግቦችና የትኩረት መስኮችን ያለመረዳት፣ ሠራተኛው በተቋሙ ስለሚከናወኑ ነገሮች ወቅታዊ መረጃ ያለማግኘት እና የመሳሰሉት በዳሰሳ ጥናቱ ከተገኙ ግኝቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ግልጽ የሆነ ተቋማዊ ባህል እንደሌለው የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ ጠንካራ ተቋማዊ ባህል ለመገንባት የአመራር ስርዓቶችን መከለስ፣ የተቋማዊ ባህል ማሻሻያ እርምጃዎችን መተግበር፣ ተቋማዊ መናበብን ማጎልበት፣ የለውጥ ሥራ አመራር ሞዴልን መቅረጽ፣ የሠራተኛ ተግባቦት ሥርዓት መዘርጋት እና የአመራር አቅም ግንባታ ፕሮግራሞችን መቅረጽ እንደሚገባ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ለተቋማዊ ባህል ግንባታ የሥራ መሪዎች ድርሻቸው የጎላ መሆኑን በመጠቆም ሠራተኛዉ  ተቋማዊ ባህልን ከስራው ጋር አስተሳስሮ መሄድ እንዳለበት አቶ አንዱአለም አሳስበዋል፡፡

በዕለቱ ከዳሰሳ ጥናቱ በተጨማሪ ተቋማዊ ባህልና ውጤቱ በሚል ርዕስ ሰነድ ቀርቧል፡፡

ሰነዱን ያቀረቡት በትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኮንስትራክሽን ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት የፕሮጀክቶች እቅድ ክትትል ዳይሬክተር አቶ ልብሰወርቅ አስፋው እንደተናገሩት የተቋምን ራዕይና ተልዕኮ በአግባቡ ለማሳካት ጠንካራ ተቋማዊ ባህል መገንባት ያስፈልጋል፡፡

እንደ አቶ ልብሰ ወርቅ ገለፃ ጠንካራ ተቋማዊ ባህል ለመገንባት የሠው ሃብት አቅምን ማሳደግ እና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ረቂቅ ዳሰሳ ጥናቱ አስፈላጊ መረጃዎች ተካተው በተቋሙ ከፍተኛ የስራ አመራር ከጸደቀ በኋላ ሁሉም ሠራተኛ እንዲያገኘው እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

4 × 3 =