ግድቡ አሁን ከያዘው በ3 እጥፍ የሚበልጥ ውሃ እንዲይዝ ይደረጋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በዘንድሮው ዓመት አሁን ከያዘው በ3 እጥፍ የሚበልጥ ውሃ እንደሚይዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጋራ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጉብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው የግድቡ ግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውንም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ለተሳተፉ እና አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን የተሠራው ሥራ ትልቅ ስኬት ቢሆንም በስኬቶች ከመኩራራት በየጊዜው አዳዲስ ግቦችን በመቅረፅ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለመውሰድ እንደሚሠራም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልፀዋል።
በዚህ ዓመት ግድቡ ከፍ እንዲል ማድረግ እና አሁን ካለው ውሃ ሦስት እጥፍ እንዲይዝ ለማድረግ የሚሠራ በመሆኑ ይህ ዓመት የግድቡ ዋነኛ ሥራ የሚሠራበት ነው ብለዋል።
በተያያዘም በዚህ ዓመት ኃይል ማመንጨት የሚጀምሩ ተርባይኖች ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተርባይኖቹ ለስድስት ወራት ሙከራ ካደረጉ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ኃይል ወደ ማመንጨት ይገባሉ ነው ያሉት።
የግድቡን የግንባታ ሂደት የጎበኙበት ምክንያት የሥራውን እንቅስቃሴ ለማየት እና ወደ ፊት በግድቡ አካባቢ ለመሠራት ለታቀዱት ከተሞች የአመቺነት ሁኔታን ለማየት እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
ግድቡ ሲሞላ ብዙ ደሴቶችን ስለሚፈጥር ከወዲሁ ያንን እያዩ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የግድቡ ሁኔታ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ ውጤታማ እንደሚሆን ለሁሉም ወገን የሚያመላክት ነው ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፣ “በየጊዜው ያንን እያረጋገጥን ስኬታችንን እውን ማድረጋችን አይቀርም” ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
0 Comments