ግድቡ በአንድ ዩኒት የኃይል ማምረት ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዩኒት የኃይል ማመንጨት ሥራውን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው እንዳመለከቱት የግድቡን ስራ በአግባብ እንዲከናወንና ለዚህ እንዲደርስ ያደረግን እንጂ ያስጀመርን ባለመሆኑ ለቀጣይ ትውልድ በማሰብ ራዕይ ሰንቀው ዲዛይን ያሰሩና ግንባታውን ያስጀመሩ መሪዎችን በስም በመጥራት አመስግነዋል።
የአንድነትና የመነሳሳት ተምሳሌት በሆነው በዚህ ሀገራዊ ፕሮጀክት ላይ የተሳተፉትን ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲሁም አስተዋፅኦ የነበራቸውን አካላትና ግለሰቦችም አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ፍላጎት ኤሌክትሪክ በማመንጨት በጭለማ የሚኖረውን ህዝብ ኑሮ የሚለውጥና ካለንበት ድህነት ማላቀቅ በመሆኑ ኃይል አመንጭቶ እንደቀደመ ፍሰቱን እንደሚቀጥል ማሳያ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አብርሃም በላይ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ያለፈበትን ሂደት በማንሳት ና ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ በመዘርዘር ፕሮጀክቱ ለህዝብና ለእውነት የቆመ መንግስት መኖሩን ማረጋገጫ ነው ሲሉ ገልፀውታል።
በፕሮጀክት አያያዝ የተከሰቱትን ጉልህ ችግሮች ከመሸፋፈን ይልቅ የተጠናና በንድፈ ሀሳብ የተመሰረተ የእርምት እርምጃዎች መወሰዳቸውንና ለመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል ማመንጨት መብቃቱን አንስተዋል።
የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ሀገር በጭንቅ ወቅት ሆና እንኳን ለአፍታም ያልተስተጓጎለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል ማመንጨት ስራ በስኬት ቢጠናቀቅም ለፍፃሜ ለማድረስ የህዝብና የመንግስት ድጋፍ እንዳይለየው ጥሪ አቅርበዋል።
በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔዎች፣ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት፣ ሚኒስትሮች፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
0 Comments