ግንባታውን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

በኮምቦልቻ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን ባለ 400/230/33 ኪ ቮ. የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ቀሪ የሲቪል እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ አስታወቀ፡፡
የጣቢያው ሳይት ተቆጣጣሪ መሃዲስ አቶ ኃይለየሱስ ስንታየሁ እንደተናገሩት እስከአሁን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችን የመገጣጠምና ወሳኝ የብረታ ብረት ስራዎች ተጠናቀዋል፡፡
የኤሌክትሮ መካኒካልና የብረታ ብረት ተከላና ለኤሌክትሪክ ገመዶች ቀበራ የሚውል ግንባታ ፣ እና ሁለት ባለ 150 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር ተከላ ሥራዎች እና ሁለት ባለ 500 ሜጋ ቮልት አምፒር መትከያ የመሰረት ግንባታም ተከናውኗል፡፡
የመቆጣጠሪያ ቤት፣ የሰራተኞች መኖሪያ ቤት፣ የጥበቃ ቤት፣የስዊች ጊር ቤት እና የፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታዎች የማጠናቀቂያ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በቀጣይም የጠጠር ንጣፍ፣ የውስጥ አጥር፣ የስዊችያርድ ግንባታ እና የኬብል ዝርጋታ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ መሃንዲሱ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ኃይለየሱስ ገለጻ ማከፋፈያ ጣቢያው 1000 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት ባለ 500 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር እና 300 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለቸው ሁለት 150 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር ይገጠሙለታል ፡፡
የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ የትናየት ይመር እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያውን ስራ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት 952 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡
ግንባታውን ሻንጋይ ኤሌክትሮ ግሩፕ የተባለው የቻይና ኩባኒያ ሲያከናውን የአማካሪነት ስራውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ ኃይል እያከናወነው ይገኛል፡፡
ከአዲስ አበባ በ350 ኪ.ሜ. ርቀት ላይበአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በኮምቦልቻ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የኮምቦልቻ ባለ 400 /230/33 ኪ.ቮ. የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ የተለያዩ የሲቪል እና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎችን በማከናወን አማካይ አፈጻጸሙ ከ48 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅ ሃያ ባለ 33 ኪ.ቮ. ወጪ መስመር ያሉት ይህ ማከፋፈያ ጠቢያ የኮቦልቻ ኢንዲሰትሪ ፓርክ፣ የኮቦልቻ -ወልዲያ ባበር ፕሮጀክት እና የኮቦልቻ ከተማ እና በአካባቢው የኃይል ፍላጎት አቅርቦት ጥያቄ ከመመሉሱ ባሻገር አስተማማኝ ተጨማሪ ኃይል እንዲኖር ያደርጋል ፡፡
0 Comments