ጊቤ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለፉት ስድስት ወራት ከዕቅድ በላይ ኃይል ማመንጨት ችሏል

Published by corporate communication on

የጊቤ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በግማሽ ዓመቱ 958 ጌጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ለማመንጨት አቅዶ 1028 ነጥብ 5 ጌጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ማመንጨቱን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሐብታሙ ገረመው አስታወቁ፡፡

ጣቢያው ያመነጨው ከዕቅዱ የ 7 በመቶ ብልጫ እንዳለው ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

ከጊቤ 3 እና ከበለስ ቀጥሎ ትልቁ የኃይል ማመንጫ የሆነው የጊቤ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 420 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ሲኖረው የሀገሪቱን የኃይል ፍላጎት ከማሟላት አንፃር የጎላ ሚና በመጫዎት ላይ የሚገኝ ጣቢያ ነው፡፡

ከሰው ኃይል ልማት አኳያም ለዘጠኝ አዲስ መሐንዲሶች እና ለአራት ቴክኒሺያኖች ለሁለት ወራት ያህል የስራ ላይ ስልጠና መሰጠቱን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የጣቢያው የጥገና ክፍል ተወካይ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ተስፋ በበኩላቸው ከኦፕሬሽን ተግባራት ጎን ለጎን ጣቢው ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል የጥገና ሥራዎች ሲከናወኑ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ዘይት እያፈሰሰ የኃይል ማመንጨቱን ስራ ያስተጓጉል የነበረውን የውሃ መቀበያ ዋና አሸንዳ እና የመቆጣጠሪያ ክፍል የአየር ማቀዝቀዣ በጥገና ክፍሉ ባለሙያዎች ተጠግኖ ወደ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ለጣቢያው የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት የሚውል 56 ዓይነት የመለዋወጫ ዕቃዎች ከውጭ መግባታቸውን የተናገሩት አቶ አሸናፊ በአሁኑ ጊዜ የአንድ ዩኒት መደበኛ ጥገና ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በ2002 ዓ.ም ተመርቆ በይፋ ስራ የጀመረው የጊቤ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሶስት ትራንስፎርመሮችን የያዘ ባለ 400 ኪ.ቮ ስዊችያርድ አለው፡፡ ከአዲስ አበባ በ250 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሠቦች እና ህዝቦች ክልል በየም ልዩ ወረዳ የሚገኘው ጣቢያው ለሰበታ፣ ሰኮሩ እና ወላይታ ሶዶ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል የሚያቀርቡ ሶስት ወጪ መስመሮችም አሉት፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

three × 3 =