ጉዳት የደረሰበትን የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር የመጠገን ሥራ እየተከናወነ ነው

Published by corporate communication on

በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሃት ቡድን በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው በምስራቅ አማራ እና በአፋር የተወሰኑ አካባቢቢዎች ላይ የተጎዱ የፋይበር ኦፒቲክስ (OPGW) መስመሮችን የመጠገን ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይበር ኦፕቲክስ የኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ገብረ መድህን እንደተናገሩት ከኮምቦልቻ- ሰመራ፣ ከሸዋሮቢት – ኮምቦልቻ፣ ከኮምቦልቻ- አላማጣ እንዲሁም ከኮምቦልቻ- አቀስታ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ምሶሶዎች አናት ላይ ተዘርግተው በሚገኙ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮቹ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መከላከያ (protection) ከመስጠት ባለፈ ለቴሌኮሙዩኒኬሽን ሥራዎች እና ከኃይል ማመንጫ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች መረጃዎችን ወደ ብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ለማድረስ  እንደሚያግዙ አቶ ኤርሚያስ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ መስመሮቹ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከሉ   ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ መረጃዎችን መሰብሰብና መመልከት አለመቻሉን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ጉዳት በደረሰባቸው መስመሮች ላይ የፋይበር ኦፕቲክስ ተከራይቶ ይጠቀም እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኤርሚያስ በደረሰው ጉዳት ምክንያትም አገልግሎቱ ተቋርጦ ቆይቷል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን መስመሮች በመጠገን ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየተሰራ እንደሆነም ሥራ አስኪያጁ አንስተዋል፡፡

የፋይበር ኦፕቲክስ የጥገና ስራ ጥንቃቄን የሚጠይቅና አድካሚ እንደሆነ ያነሱት አቶ ኤርሚያስ  አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ በወቅቱ ለማድረስ ሁሉም ሠራተኛ በከፍተኛ ተነሳሽነት፤ በመተሳሰብና በመደጋገፍ የጥገና ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ጉዳት የደረሰባቸውን የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች ለመለየት የሚከናወነው ስራ ከጥገና ስራዉ የማይተናነስ አድካሚና አስቸጋሪ በመሆኑ ‘‘OTDR (Optical Time Domain Reflector’’ በተሰኘ ማሽን በመታገዝ ጉዳቱን በመለየት የጥገና ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በአካባቢው ያለው ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘው ከረጅም ጊዜ በኋላ በመሆኑና ለጥገና ሥራ በሚል ኤሌክትሪክ በተከታታይ እንዳይቋረጥበት በማሰብ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ኤሌክትሪክ በማቋረጥ ጥገናው እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ከኮምቦልቻ- ሰመራ በተዘረጋው የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር ላይ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ በሚሆነው ላይ ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም ሁሉንም በአዲስ በመቀየር ደሴ ከተማ ከሚገኘው የኢትዮ ቴሌኮም ሰርቨር ጋር ማገናኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

ከሸዋ ሮቢት – ኮምቦልቻ በተዘረጋው የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር ላይ ደግሞ 33 ኪሎ ሜትር በሚሆነው ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 18 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን በአዲስ መቀየር መቻሉን ነው የጠቆሙት፡፡ የ15 ኪሎ ሜትሩን ቀሪ ሥራዎች በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት በሚገኙት እሁድ ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

ከኮምቦልቻ- አቀስታ ባለው የፋይበር ኦፐቲክስ መስመር ላይ 1 ኪሎ ሜትር በሚሆነው ላይ ጉዳት እንደደረሰበትም ታውቋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ15 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች እንደሚገኙ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የአማራና አፋር ክልሎችን በወረራ ይዞ በቆየባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ የማስተላለፊያ መስመሮች መካከል በ53 ነጥብ 3 በመቶው ላይ ጉዳት ማድረሱን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

5 × three =