ዶ/ር አብርሃም በላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ከነሐሴ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ያገለገሉት ዶ/ር አብርሃም በላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ፡፡
ዶ/ር አብርሃም ተቋሙን በመሩባቸው ጊዜያት የተቋማዊ ለውጥ ስራዎችን በማቀድና በመምራት ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ችለዋል፡፡
ከነበረበት የእዳ ጫና የሚያላቅቅ የብድር ማስተካከያ እንዲደረግና የተቋሙ ያልሆኑ ብድሮች ወደ ሚመለከታቸው አካላት እንዲተላለፉ ትልቅ ስራ ሰርተዋል፡፡
ለዓመታት በካሳ ክፍያ የተነሳ ሲጓተት የነበረውን የገናሌ ዳዋ 3 ፕሮጀክት ተጠናቆ ለምርቃት ዝግጁ እንዲሆን፣ የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ እና የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መልካም አፈፃፀም እንዲኖራቸውና ሰራተኛው በተቋሙ ላይ ያለው የእኔነት ስሜት እንዲያድግ ማድረግ ችለዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብም ወደ ትክክለኛ መስመር እንዲመለስ ያደረጉ፣ በፕሮጀክቱ ሳይት ላይ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ በመገኘት አፈፃፀሙን በመከታተል ድጋፍና ክትትል ያደረጉ ኃላፊ ናቸው፡፡
ተቋሙ በኮርፓሬት ቢዝነስ አስተሳሰብ እንዲመራ በማድረግ የ5 አመት ስትራቴጂ እንዲቀረፅም አድርገዋል፡፡
ለረዥም አመታት በጥገና ቆመው የነበሩ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ወደ ሀይል እንዲመለሱና በዘላቂነት የመለዋወጫ አቅርቦት መፍትሄ እንዲያገኝ የማዕቀፍ ስምምነት ስርዓት እንዲዘረጋ አድርገዋል::
በተጨማሪም አዳዲስ የገቢ ማስገኛ ስልቶችን በመቀየስ የተቋሙን የፋይናንስ አቅም ወደ ጤነኛ አቋም የሚመልሱ ስራዎችን፣ የደመወዝ ማሻሻያ፣ የግሬድማስተካከያ፣ የጥቅማጥቅም ማሻሻያ ስራዎች በተቋሙ ከሰሯቸው ስራዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ዶ/ር አብርሃም በላይ በሄዱበት ቦታ ስኬት እንዲገጥማቸው መላው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሰራተኛ እና ማኔጅመንት ይመኛል፡፡
0 Comments