የጥገና ሥራዉ የሠራተኛው አቅም የታየበት ነው- በጥገና ሥራው ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎችና አመራሮች

Published by corporate communication on

አሸባሪው የህወኃት ቡድን ውድመት ያደረሰበትን የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመጠገን በተደረገው ርብርብ የሠራተኛው የመስራት አቅም የታየበትና ከዚህም በላይ መስራት እንደሚችል የተረጋገጠበት መሆኑን በጥገና ሥራው ላይ የተሳተፉ የሥራ መሪዎችና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

በትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት የማስተላለፊያ መስመሮች የቴክኒክ ድጋፍ ኃላፊና የጥገና ስራው አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ መንግስቱ እንደገለፁት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመጠገን እና ህብረተሰቡ በአፋጣኝ ኃይል እንዲያገኝ ለማድረግ ከስምንቱ ሪጅኖች እና ከራስ ኃይል ቢሮ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ወደ ጥገና ሥራው ሲገባ ከፍተኛ ውድመት አጋጥሞ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተስፋዬ ሥራው በቅንጅት በመሰራቱ እና ለጥገና ሥራው የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችና የሰው ኃይል በማሟላት ዝግጅት በመደረጉ ህብረተሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡

ህብረተሰቡ ከነበረበት የስነ ልቦና ችግር ተላቆ ወደ ቀየው እንዲመለስ እና አካባቢውን እንዲያረጋጋ ለማድረግ ከተከናወነው ሥራ በተጓዳኝ ሠራተኛውን በማደራጀት ጥገናው በተነሳሽነት ስሜት እንዲከናወን ተቋሙ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡

እየተከናወነ ባለው የጥገና ሥራ የሠራተኛው አንድነት፣ ተነሻሽነትና አቅም የታየበት እንዲሁም ከዚህ የባሰ ችግር ቢመጣም ችግርን ተቋቁሞ ለውጤት የሚሰራ ጠንካራ ሠራተኛ እንዳለን ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊው  ገለፃ ሥራው ወደፊት ተቋሙ የሚያከናውናቸውን ትልልቅ ሥራዎች በራስ አቅም ለመስራት ልምድ የተገኘበት ነው፡፡

በሰሜን ምስራቅ ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ኃላፊ አቶ ፀሐይነህ አበበ በበኩላቸው ሠራተኛው የተለያዩ መሰናክሎችን በመቋቋም ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ ለማድረግ በቁርጠኝነት ሲሰራ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የጥገና ሥራው የሠራተኛውን አቅም ለመለየትና በራስ አቅም መስራት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው ያሉት አቶ ፀሐይነህ፡፡

በጥገና ስራው ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት ባለሙያዎች መካከል የሰሜን ምስራቅ ሪጅን የጥገና ባለሙያ የሆኑት አቶ ያረጋል ታዬ እና በትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኮንስትራክስን የራስ ኃይል ቢሮ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ፀሐዬ ማቼ በበኩላቸው ከአካባቢው መልከዓ ምድር አቀማመጥ የተነሳ ሥራው አሰልቺና አድካሚ ቢሆንም ሠራተኛው ችግሩን በመቋቋም በእልህና በቁጭት ሰርቶ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ በጦርነት ከደረሰበት ጉዳት በተጨማሪ በኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ምክንያት ለሌላ ቀውስ እንዳይዳረግ ተቋሙ አጥጋቢ ሥራ እየሰራ እንደሆነና በቀጣይ ይህን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የስራ መሪዎቹና ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

በዚህ የጥገና ስራ ተቋሙ የህዝብ አገልጋይ መሆኑን እንዳሳዩ ሁሉ በቀጣይ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ ህዝቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

10 − 3 =