የጣቢያውን ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት የሚቀርፍ ግንባታ እየተከናወነ ነው

Published by corporate communication on

በጊቤ 2ኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የተጀመረው የሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሲጠናቀቅ ያለውን የመኖርያ ቤት ችግር ሙሉ በሙሉ እንደሚቀርፍ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጊቤ 2ኛ የሠራተኞች መኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ብርሃኑ ደበላ እንደገለፁት በሚያዚያ ወር 2013 ዓ.ም የተጀመረው የመኖሪያ ቤት ግንባታ አፈጻጸሙ 18 በመቶ ደርሷል፡፡

ግንባታውን በ18 ወራት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ የታቀደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የዕቃ አቅርቦት፣ የተዳፋት ግንባታ አቃፊ ሥራዎች፣ መሰረት የማውጣትና የኮንክሪት ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

በቀጣይም ቀሪ የቁፋሮ እና የመሰረት ሥራዎችን አጠናቆ ግንባታውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለመጨረስ የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር እንዳይሆን ከወዲሁ ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ተቋራጭ የሳይት ስራ አስኪጅ አቶ አዲስ ፈንታ በበኩላቸው ፕሮጅክቱ ላይ የአናፂና የግንብ ሥራ ባለሙያና የጉልበት ሰራተኛ እጥረት ችግር ቢኖርም ከተቋሙ ጋር በተገባው ውል መሰረት ግንባታውን ሰርቶ ለማስረከብ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከመኖሪያ ቤት በተጨማሪ የቢሮ፣ የስፖርት መዝናኛ ማዕከል፣ የክሊኒክ እና የትምህርት ቤት ግንባታም ያካተተ ሲሆን ለግንባታው 380 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡ 

የፕሮጀክቱን ግንባታ ዓይናለም ጋሻው እና ሉሲ ኢንጅነሪንግ የተባሉ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች እያከናወኑት ሲሆን ፕሮጀክቱ 100 ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች ጊዚያዊ የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

11 + eighteen =