የጊንጪ ባለ 230/15 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ተመረቀ

Published by corporate communication on

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የጊንጪ ባለ 230/15 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን በዛሬው ዕለት በይፋ  መርቀዋል።

በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያው በአካባቢው የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታትና  በአካባቢው ኢንቨስትመንት እንዲስፋፉ ለማድረግ ያግዛል።

መንግስት በመላው ኢትዮጵያ የልማት ችግሮችን ለመፍታትና የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የማከፋፈያ ጣቢያዎች  ተገንብተው እየተመረቁ መሆናቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የአካባቢውን ነዋሪዎች በልማቱ ተጠቃሚ ስለሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ጣቢያው  የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አንዱ አካል ለሆነው  ለወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ  የራሱን አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡        

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው  ማከፋፈያ ጣቢያው እስከ 100 ሜጋ ዋት ኃይል የመሸከም አቅም ያለውና ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር  ትራንስፎርመሮችየተገጠሙለት እንዲሁም  አስር ባለ15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት ብለዋል፡፡  

ማከፋፈያ ጣቢያው ለጊንጪ ከተማና አካባቢው ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ከማቅረብ ባለፈ በአካባቢው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ያግዛል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃይል እንዲያገኝ ለማድረግና የኃይል ተደራሽነት ችግርን ለመፍታት  ከተለያዩ የኃይል ምንጮች አስከ 20 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያዎች የመነጨውን ኃይል ወደ ውጤት ተጠቃሚው ለማድረስ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ  በቀጣይ በሸኮቴ አካባቢ የሚገነባው ማከፋፈያ ጣቢያ የምዕራብ ሸዋን የኃይል ችግር  ሙሉ በሙሉ ይፈታል ሲሉ ገልፀዋል።

በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ  የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ ጨምሮ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ አባ ገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል፡፡    

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

16 + 6 =