የጊቤ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግድብ ውሃ መለቀቅ ተጀመረ

Published by corporate communication on

የጊቤ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ በክረምቱ ዝናብ እየሞላ በመምጣቱ ውሃ መለቀቅ ተጀምሯል፡፡

ከግድቡ በየደረጃው የሚለቀቀው ዉሃ በታችኛው ተፋስስ ላይ ቅፅበታዊ ጎርፍ እንዳይከሰት ለመቆጣጠር ነው፡፡

ወደ ግድቡ የሚገባውን ውሃ ሁሉ እንደመጣ ላለመልቀቅና የተመጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ሊያጋጥም የሚችለውን ጉዳት ለማስቀረት ከአደጋ መከላከልና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጋር በመሆን በተፋሰሱ የታችኛው ክፍል የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩና መልዕክቶች ሲተላለፉ ቆይተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግድቡ በተከታታይ በቀን በአማካይ 40 ሳ.ሜ. ከፍታ ያለው ውሃ እየያዘ በመሆኑ በመካከለኛ ከፍታ ላይ የሚገኙ የግድቡን ውሃ ማስተንፈሻዎች በመክፈት ትላንት ከእኩለ ቀን ጀምሮ ለስድስት ሰዓታት በሰከንድ ወደ 2ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ መልቀቅ ተጀምሯል፡፡

ዛሬም በተመሳሳይ ውሃ የመልቀቅ ሂደቱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደግድቡ የሚገባውን ውሃ ታሳቢ ያደረገ ተጨማሪ ውሃ ሊለቀቅ ስለሚችል አሁንም በኦሞ ጊቤ የታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ ነዋሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዲችሉ የአካባቢው አመራሮች ተገቢውን መልዕክት እንድታስተላልፉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ነሐሴ 06 ቀን 2012 ዓ.ም.

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

five × five =