የጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በርካታ የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራዎች ማከናወኑን ገለፀ

የጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለፉት ስድስት ወራት ስኬታማ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች ማከናወኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ንጉሴ አስታውቁ፡፡
በስድስት ወራት ውስጥ 534 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ለማመንጨት ታቅዶ 600 ጌጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በማመንጨት የዕቅዱን 120 በመቶ ማሳካት መቻሉን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
ጣቢያው 230/132 ኪ.ቮ አቅም ያለው ስዊች ያርድ ባለቤት ሲሆን ለጌዶ፣ ሰበታና ሰኮሩ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኤሌክትሪክ የሚያቀርቡ ሶስት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡
ከኦፕሬሽን ሥራዎች ባሻገር በማቀዝቀዣ፣ በዲዝል፣ በስካዳ ሲስተም እና በስዊችያርድ ላይ የጥገና ሥራዎች የተከናወኑ መሆኑን አቶ ደሳለኝ ገልፀዋል፡፡
በብልሽት ምክንያት ለሥራ እንቅፋት ሆኖ የቆየውን የዩኒት አንድ ሰርቨር የኮምፒውተር ሰሌዳ ወይም ስክሪን በመጠቀም እንደገና አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡
በስዊችያርድ ላይ የሞደፊኬሽን ሥራዎች በማከናወን ስዊች ያርድ ላይ ያጋጥም የነበረውን ተደጋጋሚ የኃይል መቋረጥ ማስቀረት መቻሉንም ነው አቶ ደሳለኝ የተናገሩት፡፡
በተጨማሪም ለ8 ዓመታት ያህል ተበላሽቶ የነበረ ተጠባባቂ ዲዝል ጀነሬተር በመጠገን እንዲሁም የቬንትሌሽን ሲስተም ላይ የጥገናና የሞደፊኬሽን ሥራዎች በማከናወን አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
የውሃ መውጫ (Tailrace Outlet) እና የግድቡ የታችኛው የውሃ መልቀቂያ (Bottom Outlet) ክረምት ከመግባቱ በፊት አስቸኳይ ጥገና እንዲከናወንላቸው አቶ ደሳለኝ ጠይቀዋል፡፡
በ1996 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ግልገል ጊቤ አንድ የውሀ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 184 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው፡፡
0 Comments