የገናሌ ዳዋ IIIየኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በጥሩ ሁኔታ ውሃ በመያዝ ላይ ይገኛል

Published by corporate communication on

የሁለት ክረምት ባለቤት በሆነው ገናሌ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የገናሌ ዳዋ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በጥሩ ሁኔታ ውሃ በመያዝ ላይ መሆኑን የፕሮጀክቱ ተወካይ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴወድሮስ ሁሴን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የግድቡ የውሃ መጠን 88 ሜትር ከፍታ የደረሠ መሆኑን ያስታወቁት ተወካይ ሥራ አስኪያጁ የሚፈለገው ውሃ መጠን ላይ ለመድረስ 10 ሜትር ከፍታ ብቻ መቅረቱንና ይህም ከፍታ በአንድ ወር ውስጥ ሙሉ በመሉ ይሞላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡

የመካኒካል እና ኤሌክትሪካል ሥራዎችን መሰረት ያደረገ የደረቅ ሙከራ መደረጉን የተናገሩት አቶ ቴወድሮስ በኃይል ማስተላለፊያው ላይ ያሉ የኮሚዩኒኬሽን መስመሮች ከተስተካከሉ በኋላ ውሃን በመጠቀም የመጨረሻውን ኃይል የማመንጨት ሙከራ እንደሚከናውንም ነው የገለፁት፡፡

በአጠቃላይ ግድቡ 2.57 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ እንደሚጠበቅበት እና በአሁኑ ጊዜም 1.768 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ መቻሉን አቶ ቴወድሮስ አስታውቀዋል፡፡

በታችኛው የወንዙ ተፋፈስ ላይ የሚገኙ የህብረተሠብ ክፍሎች እንዳይጎዱም በዘመናዊ መልኩ በተገነባ ውሃ ማፋሳሻ  በሰከንድ 1. 5 ሚሊየን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ እየተለቀቀ መሆኑን እና ይህም በግድቡ ሙሌት ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ እንደማያሳርፍ አቶ ቴዎድሮስ አብራርተዋል፡፡

እንደ ተወካይ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር የአካባቢው ወጣቶችን በማደራጀት በዓሳ ሃብት ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ከክልሉ የግብርና ቢሮ ጋር በመቀናጀት በግድቡ ላይ ጥናቶች ተጀምረዋል፡፡

 ከ50 ኪ.ሜ በላይ የሚያካልለው የገናሌ ዳዋ III ኃይል ማመንጫ ግድብ የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር ከመጠበቅ አንፃርም የማተይካ ሚና ይኖረዋል፡፡ 

ፕሮጀክቱ ግንባታው ተጠናቆ ኃይል ለማመንጨት በመቃረቡ የኃይል ማመንጫ የኦፕሬሽን እና የጥገና ቴክኒሺያኖች ቀድመው በቦታው መመደባቸውን ያስረዱት ተወካዩ ይህም የኃይል ማመንጫውን  ሁኔታ ቀድሞ በመረዳት ውጤታማ የኦፕሬሽን ሥራ ለማከናዎን ይረዳል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ አሁን ላለበት ደረጃ የደረሰው በርካታ የሲቪል፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና ስቲል ስትራክቸር ሥራዎችን በማከናወን ሲሆን የዋና ግድብ (Main Dam)፣ የውሃ መልቀቂያ ዋሻ (Water Release Tunnel)፣ የውሃ ማስተንፈሻ (Spillway)፣ የውሃ ማስገቢያ ዋሻ (Power Intake) እና የውሃ ማስተላለፊያ ዋሻ (Hardrace Tunnel) የግንባታ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡

የሦስቱ ዩኒቶች የኤሌክትሮ ሜካኒካል የተከላ ሥራ ተጠናቆ የፍተሻ ሥራ በመከናወን ላይ  ሲሆን የመቆጣጠሪያ እና የዲዝል ጀነሬተር ቤት ግንባታ የቀለም ቅብ እና የወለል ንጣፍ ሥራዎች

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በጉጂ እና ባሌ ዞኖች በሚገኙት የመዳ ወላቡና ጎሮዶላ ወረዳዎች አዋሳኝ ቦታ ላይ እየተገነባ ያለው ይህ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ በ630 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ 

የግንባታ ሥራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 254 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አማካይ ዓመታዊ የኃይል ምርት አቅሙም በሰዓት 1640 ጊጋ ዋት ነው፡፡

የፕሮጀክቱን የሲቪል እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን እየሰራ የሚገኘው ሲጂጂሲ (CGGC) የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ሲሆን የማማከር (consultant) ተግባሩን ደግሞ የአሜሪካው ኤም. ደብሊው. ኤች (MWH) ከሃገር በቀሎቹ አኪዩትና ኢንቲግሬትድ ጋር በጥምረት በመሆን እየሰሩት ይገኛሉ፡፡ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ሰዓት ለ390 ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለ የደረሰን መረጃ ገልፃል፡፡

ግንባታው በ2003 ዓ.ም የተጀመረው ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪው 451 ሚሊዬን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ከቻይናው ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ (Exim Bank) በብድር የተገኘ ነው፡፡ ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ በቅርቡ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

seven − two =