የደጀን ደብረ ማርቆስ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ የሲቪል ሥራ አፈጻፀም 16 በመቶ ደረሰ

በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የተጀመረው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ የሲቪል ሥራ አፈጻፀሙ 16 በመቶ ደርሷል፡፡
ከአዲስ አበባ በ229 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደጀን ከተማ የተጀመረው የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታ በአሁኑ ወቅት የትራንስፎርመር መትከያ ስፍራ መሰረት ተጠናቋል።
የደጀን ደብረማርቆስ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ እና የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ታምራት እንደገለፁት የፕሮጀክቱ የቁፋሮ፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የአጥር እና የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታዎች ሥራ እየተከናወኑ ነው።
ለማከፋፈያ ጣቢያው ከደብረ ማርቆስ – ደጀን የሚደርስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር ሰርኪዩት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር እንደሚዘረጋ ተገልጿል፡፡
የሲቪል ሥራ አፈጻፀሙ 16 በመቶ የደረሰ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በደጀን እና ደብረ ማርቆስ ከተሞች ለተገነቡት ፋብሪካዎች እና ለአካባቢው ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል በአስተማማኝ ሁኔታ ለማቅረብ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
የደጀን ደብረማርቆስ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ እና የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት በተቋሙ የራስ አቅም (Own force) የሚገነባ ነው።
ፕሮጀክቱን በ14 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን ለግንባታውም ከ133 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቧል፡፡
0 Comments