የዓለም የህጻናት ቀንን በማስመልከት በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ የተላለፈ መልዕክት
በዋና ዋና የክልል ከተሞችን ጨምሮ በመዲናችን አዲስ አበባ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ምክንያት ወደ ጎዳና የወጡና ለበርካታ ችግሮች የተጋለጡ ህጻናትን መመልከት የተለመደ ክስተት ሆኗል። ህፃናትን ወደ ጎዳና የሚያስወጡ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋንኛ የሚጠቀሰው ድህነት፣የትዳር መፍረስ፣ በወላጆች ሞት ሳቢያ የሚከሰት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር፣ ህገወጥ የህጻናት ዝውውር፣ ዝምድናን ተገን በማድረግ “አስተምራቸዋለሁ” በማለት ህጻናትን ከቤተሰብ መነጠል በአብዛኛው ለህፃናት ጎዳና መውጣት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡
እድሜያቸው በአማካኝ ከሰባት እስከ አስራ ሁለት የሆኑ ህፃናት ምግብና መጠለያ ስለማያገኙ ረሃባቸውን ለማስታገስና ብርዱንና ፀሐዩን ለመቋቋም ቤኒዚንና ማስቲሽ ይስባሉ። አለፍ ሲል ደግሞ ቀን ሲሸከሙ፣ ሲለምኑ እና በተለያዩ ዘዴዎች (ቅሚያና ዘርፊያን ጨምሮ) በሚያገኙት ገንዘብ የዕለት ጉርሳቸውን ያገኛሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ1954 በወጣውና በ1959 በፀደቀው አለም አቀፍ የህጻናት መብቶች ድንጋጌ ላይም ለህፃናት ልዩ እንክብካቤና እርዳታ ማድረግ የቤተሰብም የማህበረሰብም ግዴታ መሆኑ በግልፅ ተቀምጧል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ 2012 ለአለም አቀፉ የህጻናት መብቶች ስምምነት ኮሚቴ ላቀረበችው የ4ኛው እና የ5ኛው የህጻናት መብቶች አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት አድርጎ በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ኢትዮጵያ የህጻናትን የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች ለማሻሻል ትኩረት ሰጥታ በመስራቷ ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት ሞት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፤ ለትምህርት የደረሱ ህፃናት የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ተሳትፎ ጨምሯል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የህጻናትን መብት ለማስጠበቅ እያደረገች ያለችው ጥረት በኮሚቴውም አድናቆት ተችሮታል፡፡
ይሁን እንጂ፣ አሁንም መንግስት አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ብሔሮችና ብሄረሰቦች እንዲሁም ከመሃል ሀገር ራቅ ባሉ የገጠር አካባቢዎች በድህነትና በአስቸጋሪ ሁኔታ ያሉ ህጻናትን ኑሮ ለማሻሻል መንግስት ያደረገው ጥረት በሪፖርቱ አለመቅረቡ ትልቅ ክፍተት በሚል ተገምግሟል።
ዘመድ ነን በሚል ህጻናቱን ከወላጆቻቸው “እናስተምራቸዋለን” በማለት ከወሰዷቸው በኋላ ከናካቴው ሳያስተምሩ አሊያም ቀን ቀን እየሰሩ በማታው የትምህርት ጊዜ እንዲማሩ ይደረጋሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በህጻንነታቸው አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ የሆነ ጥቃት እንዲደርስባቸው ያደርጋል፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በህግ ብቻ መከላከል አይቻልም። በመሆኑም ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ይህን አይነት ጉዳይ በሚፈጽሙና በሚያስፈጽሙ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ይገባል።
ቤተሰብም የደላሎችን ባዶ ተስፋ ማድመጥ የለበትም። ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ጉዳዩን ትውልድን ከመታደግና የነገ አገር ተረካቢዎችን ከመፍጠር ጋር በማያያዝ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል፡፡
ሃገራችን የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽን ከተቀበለችና ከፈረመችበት ከ1984 ዓ.ም ወዲህ ለአፈፃፀሙ የሚረዱ የተለያዩ ተቋማዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ህፃናት በየደረጃው የመብቶቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ብሎም በአስከፊ ህይወት ውስጥ ያሉ ህጻናትን በአሳሳቢ ደረጃ ያሉትን የጎዳና ህጻናት በዘላቂነት የሚቀይር እና የሚታደግ ስራዎችን ተግብሯል።
በመሆኑም ለ31ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው የዓለም የህፃናት ቀን የተመራበትን “A Day to Reimagine the Future ” እና በሀገራችን ለ15ኛ ጊዜ “ትዉልድን እንቅረጽ ሀገርን እንገንባ !!” የሚለውን የዘንድሮውን መሪ ቃል መሰረት በማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ስሜት ህጻናት ከሃገሪቱ ዘላቂ ልማትና እድገት ዋነኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በየደረጃው የህጻናትን ተሳትፎ ለማጎልበት እንዲረባረቡ እንዲሁም አቅም በፈቀደ መጠን የህፃናትን ፍላጐት በማሟላት፣ ከጥቃትና ብዝበዛ በመጠበቅ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን በመደገፍና በመንከባከብ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ማሳሰቡን እንደመነሻ ወስደን፤ እኛም እንደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም ህጻናት የተሟላ ስብዕና ተላብሰው እንዲያድጉ፣ መብታቸው እንዲከበርና ደህንነታቸው እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር መልካም ስነምግባር የተላበሰ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት የሁሉም አካላት ኃላፊነት በመሆኑ በየኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ በቀጣይ ለሠራተኞች መኖሪያ ቤት ተብለው በሚገነቡ ካምፖችም ጭምር ህጻናትን ታሳቢ ያደረገ የመጫወቻና የማቆያ ቦታን ከማመቻቸት ጀምሮ በርካታ በህጻናት ዙሪያ ሊሠሩ የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን ከግንዛቤ ማስገባት ይኖርብናል፡፡
በመሆኑም በሌሎችም የስራ ቦታዎች የህጻናት ማቆያን ማቋቋም የሴት ሠራተኞችን ጫና በመቀነስ ሴቶች በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከማስቻሉም ባለፈ ህጻናት ከፍተኛ እርካታ እንዲኖራቸው፣ ከማህበረሰብ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸውን ህጻናት በመፍጠር ጤናማ የሆነ ዜጋን ከማፍራት አኳያ ተቋማችንም ኃላፊነቱን መወጣት ይገባል እያልን ለችግረኛ ህጻናትም በሰራተኞችና በስራ መሪዎች መዋጮ የሚደረገውንም ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል ያለብን በመሆኑ “አንድን ልጅ መደገፍ ሀገርን መደገፍ” እንደሆነ ተገንዝበን ሁላችንም የበኩላችንን ኃላፊነት እንድንወጣ አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡
0 Comments