የወልዲያ ባለ 230/33/15 ኪ.ቮ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀመረ

Published by corporate communication on

በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወኃት ቡድን ሙሉ በሙሉ ተነቅሎ የተወሰደውን የወልድያ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ በአዲስ ማከፋፈያ ጣቢያ ለመተካት የሚያስችል ፕሮጀክት የግንባታ ስራ ተጀምሯል።

የፕሮጀክቱ የሲቪል ስራዎች ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ከፈለኝ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት ከነበረው ተንቀሳቃሽ ጣቢያ በተለየ መልኩ በቋሚ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚከናወን ይሆናል።

የወልድያ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ወልድያ ከተማና አካባቢውን ጨምሮ በአብዛኛው በሰሜን ወሎ ዞን ስር ለሚገኙ አስር ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ይሰጥ ነበር።

ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያው ከዚህ በፊት አገልግሎት ይሰጣቸው ለነበሩ አካባቢዎች በፍጥነት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እንዲቻል በወልዲያ ከተማ እየተገነባ ከሚገኘው ባለ 400 ኪሎ ቮልት አዲስ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ላይ አንድ ቤይ በማንሳት በዚህ ፕሮጀክት ለመግጠም መታቀዱን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ የስቲል ስትራክቸር ዕቃዎች የሚቀመጡባቸውና የሚተከሉባቸው የመሰረት ስራዎች ተጠናቀዋል ብለዋል፡፡

ስቲል ስትራክቸር የመትከል ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን በአሁን ሰዓት የፕሮጀክቱ የሲቪል ግንባታ አማካይ አፈፃፀም 35 በመቶ ደርሷል፡፡

እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ በአሁኑ ሠዓት የመቆጣጠሪያ ቤቱ የዲዛይን ሥራ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ዲዛይኑ እንደተጠናቀቀ የመቆጣጠሪያ ቤቱን የመገጣጠም ሥራዎች በቀጣዮቹ ወራት ፕሮጀክቱን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው፡፡

የአካባቢው ወጣቶች አሸባሪው የህወኃት ቡድን በአካባቢው ባደረሰው ጉዳት እልህና ቁጭት በፕሮጀክቱ ላይ መስራት ካለባቸው ሰዓት በላይ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሳይጠይቁ እየሰሩ መሆናቸውንና ፕሮጀክቱ በተያዘለት መርሃ ግብር መሠረት እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ያላቸውን አቅም አሟጠው እየሰሩ መሆናቸውን አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ – ሜካኒካል ሥራዎች የሳይት አስተባባሪ አቶ አሊ ከሚል በበኩላቸው ጣቢያው አንድ ባለ 63 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር እንደሚገጠምለትና ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 5 ባለ 33 ኪ.ቮ እና 6 ባለ 15 ኪ.ቮ ወጭ መስመሮች እንደሚኖሩት ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያው አገልግሎት ያገኙ ለነበሩ እንደ ጭፍራ፣ ጎብየ፣ ቆቦ፣ ሮቢት እና ለሌሎች የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰጥ ይሆናል።

በትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት የማስተላለፊያ መስመሮች የጥገና ቴክኒክ ድጋፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንግስቱ እንደገለጹት በአሸባሪው የህወኃት ቡድን ዘረፋ የተፈጸመበትን የወልድያ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ በአዲስ ለመገንባት እየተከናወነ ላለው ስራ የሚያስፈልጉ ዕቃዎች በትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ስራ ጽ/ቤት አማካኝነት እየቀረቡ ነው፡፡

የፕሮጀክቱ የግንባታ ስራ በተቋሙ ትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኮንስራክሽን የራስ ኃይል ቢሮ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ለሥራው የግብዓት አቅርቦቱን ሳይጨምር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ዕቅድ መያዙን ለማወቅ ተችሏል።

ፕሮጀክቱን በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል፡፡

ሙሉ በሙሉ በአሸባሪ ቡድኑ የተወሰደውን የወልዲያ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያን ወደነበረበት ለመመለስ እና በአዳዲስ ዕቃዎች ለመተካት በትንሹ እስከ 200 መቶ ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ከዚህ በፊት መገለጹ ይታወሳል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

14 + three =