የወላይታ ሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያ የሙከራ (commissioning) ስራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል

የወላይታ ሶዶ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኮንቨርተር ስቴሽን ፕሮጀክት የሙከራ ስራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ፡፡
በፕሮጀክቱ የሰብሰቴሽን ኢንቻርጅ ባለሙያው አቶ ሃብታሙ ግርማ እንደገለፁት የኮንቨርተር ጣቢያውን የግንባታ ስራ በማጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት የኮሚሽኒንግ ስራው በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ከወላይታ ሶዶ ከተማ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተገነባ የሚገኘውን የኮንቨርተር ጣቢያ ፕሮጀክት የሙከራ ስራ በቅርቡ በማጠናቀቅ የፍተሻ ስራውን ለመጀመር እንቅስቃሴ በመደረገ ላይ እንደሚገኝም አቶ ሃብታሙ ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ሃብታሙ ገለፃ የኮሚሽኒንግ ስራው ከስራ ተቋራጩ፣ ከአማካሪ ድርጅቱ እንዲሁም ከተቋሙ የተለያዩ የስራ ክፍሎች ከተውጣጡ ባለሙያዎች በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የኮንቨርተር ሰቴሽኑ ከወላይታ ሶዶ ነባሩ የማከፋፈያ ጣቢያ የወጡ አራት ባለ 400 ኪሎ ቮልት ገቢ መስመሮች እንዳሉት ነው ባለሙያዉ የጠቆሙት፡፡
የኮንቨርተር ስቴሽኑ በድዛይን፣ በቴክኖሎጂ እና በአይነቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው እንደሆነ ያነሱት አቶ ሃብታሙ ይህም ቀጥተኛ ዥረት (Directe current) መሆኑ እና 12 ኮንቨርተር ትራንስፎርመሮች የተገጠሙለት በመሆኑ ከሌሎች ማከፋፈያ ጣቢያዎች ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ይህ ባለ 500 ኪ.ቮ የኮንቨርተር ጣቢያ ሁለት ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ወደ ማስተላለፊያ መስመር የማሻገር አቅም ያለው ሲሆን የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ኬንያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ታንዛንያንም ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
የኢትዮ- ኬንያ የማስተላለፊያ መስመርና የኮንቨርተር ጣቢያ መገንባት ኢትዮጵያ ከክፍለ አህጉራት ጋር የምታደርገውን የኃይል ትስስር በማጠናከር የሃገሪትን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል፡፡
የፕሮጀክቱን የግንባታ ስራ ሲመንስ የተሰኘ የጀርመን ኩባንያ በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በማማከር ስራው ላይ ደግሞ ትራክ ቤል የተሰኘ የጆይንት ቬንቸር ኩባንያ ተሳትፎበታል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል በመገንባት ላይ የሚገኘው የኢትዮ -ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር እና ኮንቨርተር ስቴሽን ፕሮጀክት የግንባት ስራ ቢጠናቀቅም ወደ አገልግሎት ለማስገባት የዚህ ፕሮጀክት አካል የሆነውንና በኬኒያ መንግስት በኩል እየተገነባ የሚገኘውን ፕሮጀክት መጠናቀቅ መጠበቅ እንደሚያስገድድ ነው የተገለፀው፡፡
የኮንቨርተር ስቴሽኑ ከአለም ባንክና ከአፍሪካ ልማት በብድር በተገኘ ከ285 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በጀት ተይዞለት በመከናወን ላይ የሚገኝ መሆኑን ከፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ ያለመክታል፡፡
ከዚህ ውስጥም 243 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላሩ በአለም ባንክ እንዲሁም ቀሪው ከ42 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላዩ ደግሞ በአፍሪካ ልማት ባንክ የሚሸፈን ነው ተብሏል፡፡
የኮንቨርተር ስቴሽኑ ፕሮጀክት የግንባታ ስራ በ2009 ዓ.ም በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
0 Comments