የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ በመፋጠን ላይ ነው

Published by corporate communication on

በኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘውን የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እየተፋጠነ እንደሚገኝ የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡

ምክትል ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር አባይነህ ጌትነት እንዳሉት ፕሮጀክቱ ከፋይናንስ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የታሰበውን ያህል በፍጥነት ባይጓዝም ወሳኝ የሚባሉ የተለያዩ ሥራዎች ግን ተሰርተዋል፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በግንባታ ሂደት ላይ ለሚገኘው ለዚህ ፕሮጀክት መንግስት ትልቅ ትኩረት በመስጠቱና የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ በመቻሉ በተያዘው መርሃ ግብር ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአብዛኛው ከግድቡ ግንባታ ጋር የተያያዙ የወንዙን ተፈጥሯዊ አቅጣጫ የማስቀየስ፣ የዋና ግድብና የኃይል ማመንጫ ቤቶች (power houses) ግንባታ የመሰረት ቁፋሮ የተከናወነ ሲሆን የቁፋሮ ስራዎቹ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው የዋናው ግድብ የኃይል ማመንጫ ቤት መሰረት የአርማታ ኮንክሪት RCC ሙሌት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በአሁን ሰዓት የሠራተኞች መኖሪያ ቤቶችና ቢሮዎች እንዲሁም መንገዶች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡

እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የብረታ ብረትና ሜካኒካል ስራዎች በጨረታ ሂደት ላይ ቢሆኑም የግድቡ ውሃ ማስተንፈሻ ቁፋሮ ግን ከሌሎች የሲቪል ስራዎች ጋር ጎን ለጎን እየተከናወነ በመሆኑ ፕሮጀክቱ በተያዘው መርሃ ግብር ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ተነስቶ ፕሮጀክቱ ድረስ የሚደርስ የ400 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር ዝርጋታ እና የስዊች ያርድ ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ ተጠናቋል፡፡

ለፕሮጀክቱ የተገነባው 80 ኪ.ሜ. የሚሸፍን መንገድ የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ሁለት ወረዳዎችን የሚያገናኝ 170 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይ እንዲሁም የትምህርት ቤቶችና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታና የማስፋፊያ ስራዎች ተከናውነው ለማህበረሰቡ መተላለፋቸውን አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ኃይል ከማመንጨት በተጨማሪ 129 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ሰው ሰራሽ ሀይቅ የሚፈጥር ነው፡፡

በተጨማሪም በአካባቢው ካለው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ጋር በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ስራ ከፍተኛ የቱሪዝም ማዕከል በመሆን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ እንደሚያበረክት ይታሰባል፡፡

የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀከት የማመንጨት አቅሙ 2160 ሜጋ ዋት ሲሆን በዓመት በአማካይ 6460 ጊጋ ዋት ሰዓት እንዲያነጭ ታስቦ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡

ይህም በማመንጨት አቅሙ በሀገሪቱ ካሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያስችለዋል፡፡

የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታውን የሲቪል ስራ የቀድሞ ሳሊኒ የአሁኑ ዊ ቢዩልድ እያከናወነ ሲሆን ለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጭ 2 ነጥብ 525 ቢሊየን ዩሮ ተመድቦለታል፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 39 በመቶ ደርሷል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

4 × five =