የኤሌክትሪክ ኃይልን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ማድረግ ይገባል – የአብክመ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር

የጃዊ – በለስ ባለ 132/33 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ትናንት ተመርቋል፡፡
በምርቃት ሥነ – ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅሙን በየጊዜው እያሳደገ የሀገሪቱን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ያለው ሰራ የሚበረታታ ነው፡፡
ይሁን እንጅ በክልሉ የሚስተዋለውን የኃይል ፍትሀዊነትና የተደራሽነት ችግር በመቅረፍ ለሚነሱ የኃይል ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
በኃይል ተደራሽነት ችግር ክልሉ በተለያየ መልኩ መጎዳቱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተደድሩ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን ችግሮቹ እየተቀረፉ መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡
በክልሉ የተገነቡትም ሆነ ወደፊት የሚገነቡት ኢንደስትሪዎችና ፋብሪካዎች የኃይል አቅርቦት ስለሚያስፈልጋቸው ትኩረት ሰጥቶ በመስራት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን ከ50 በመቶ በታች እንደሆነም የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ የሚገባዉን እንጅ ከሚገባው በላይ ኃይል እየጠየቀ አይደለም ብለዋል።
የበለስ ጃዊ ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ መገንባት ባለሃብቶች ወደ አካባቢው በመግባት በአግሮ ፕሮሰሲንግ ላይ እንዲሳተፉ ዕድል ስለሚፈጥር እና ለወጣቶችም ሰፊ የስራ ዕድል ስለሚከፍት ማከፋፈያ ጣቢያው ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ነው አቶ አገኘሁ የገለፁት፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ብቻ መገንባቱ ፋይዳ ስለሌለው የሚመለከተው አካል የማሰራጫ መስመሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመገንባት በጃዊ ከተማና አካባቢው የሚስተዋለውን የኃይል ችግር በአፋጣኝ እንዲፈታ አሳስበዋል፡፡
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ መገንባት ስኳር ፋብሪካዎች የሚገጥማቸውን የኃይል አቅርቦት ለመፍታትና ለጃዊ ከተማና አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል በተገቢው ሁኔታ ለማድረስ ያግዛል ብለዋል፡፡
ጣቢያው ከበለስ ስኳር ፋብሪካ ተረፈ ምርት የሚመነጨውን ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት በማስገባት የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ ያግዛል፡፡
የመነጨውን ኃይል በአግባቡ ለተጠቃሚው ለማድረስ የማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በስፋት መገንባት እንደሚያስፈልግም ዶ/ር ስለሺ አስታውቀዋል፡፡
በአምስት ዓመት ውስጥ “ብርሃን ለሁሉም” የሚለውን ፕሮግራም ለማሳካት በግሪድና ከግሪድ ውጭ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በመከናወን ላይ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ሀገሪቱ ለጀመረችው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መዋቅራዊ ሽግግር የሚውል የኤሌክትሪክ ኃይል ከተለያዩ የኃይል ምንጮች ለማምረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ለአንድ ሀገር እድገትና ከኋላ ቀርነት ለመላቀቅ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ መንግስት ለዘርፋ ትኩረት በመስጠት በርካታ መዋዕለ ነዋይ መድቦ የኃይል መሰረተ ልማቶችን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሠጥቶት በመሰራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አሸብር ገለፃ ከአዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጨማሪ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትን የማዘመንና አቅም የማሳደግ ሥራም እየተከናወነ ነው፡፡
በሀገሪቱ አሁን ያለውን 4 ሺህ 400 ሜጋ ዋት አጠቃላይ የማመንጨት አቅም በቀጣዮቹ ሥስት ዓመታት ወደ 12 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ስራ እስፈፃሚው ጠቁመዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ብቻ ፋይዳ እንደሌለው የተናገሩት አቶ አሸብር የመነጨውን ኃይል ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርሱ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታን ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
397 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባው የበለስ- ጃዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ የፋይናንስ ምንጩ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን የማማከርና የግንባታ ስራውም በተቋሙ የራስ ኃይል የተከናወነ ነው።
0 Comments