የኢንዱስትሪ ፍሰቱን ታሳቢ ያደረጉ የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው

በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ በመምጣቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚያሳድጉ መሠረተ ልማቶችን የመገንባትና አቅም የማሳደግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን እና ጥገና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ዳይሬክተር አቶ ውበቱ አቤ እንደገለፁት ከአሁን በፊት በተዘረጋው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በክልሉ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል ፈላጊ ደንበኞችን ጥያቄ ማስተናገድ አልተቻለም፡፡
ባህርዳር ላይ ባለ 400/230 /132 እና 66 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ቢገነባም ተጨማሪ የትራንስፎርመር አቅም ማሳደግ እና የማሻሻያ ሥራ ይፈልጋል ብለዋል።
ይሁንና የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት በአዘዞ – ጭልጋ ፣ በለስ – ጃዊ እና ደጀን – ደብረ ማርቆስ አዳዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ግንባታቸው እየተከናወነ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የቡሬና ባህርዳር ኢንዱስትሪ ዞኖችን ጨምሮ ጥናታቸው የተጠናቀቀ የኤሌክትሪክ ማከፋፊያ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ስለሆነም ይላሉ ዳይሬክተሩ በውጭና በውስጥ አቅም የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ለይቶ ወደ ሥራ በመግባት የህብረተሰቡን ጥያቄና የኢንዱስትሪ ፍሰቱን ማስተናገድ የሚችል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለመዘርጋት ተቋሙና ክልሉ በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
0 Comments