የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒግ (ኢ.አር.ፒ) መሰረተ ልማት ዝርጋታና አቅም ግንባታ ስምምነት ተፈረመ

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒግ (ኢ.አር.ፒ) የተሰኘ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ዝርጋታና አቅም ግንባታ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም ተፈራርመዋል፡፡

ሥምምነቱ በዋናነት የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒግ (ኢ.አር.ፒ) የአሰራር ሥርዓትን ከተቋሙ የሥራ ባህሪ አንፃር የመተግበር እና የማዘመን ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ እንደተናገሩት ሥምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢ.አር.ፒ የአሰራር ሥርዓትን ከሰባት ዓመት በላይ የተገበረውና ውጤታማ አፈፃፀም ያስመዘገበበት በመሆኑ ተቋሙ በቀላሉ ወደ ትግበራ እንዲገባ እና የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግብ ይረዳዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት የሚያንቀሳቅስ ተቋም ቢሆንም እስካሁን ግን ሀብቱን የሚያስተዳድርበት ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የአሰራር ሥርዓቶችን እየተገበረ እንዳልነበረ ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግን ተግባራዊ ማድረጉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ተቋም ለመፍጠር እንደሚያግዝ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ፕሮጀክቱ በሀገር በቀል ተቋም እንዲከናወን ሥምምነት ላይ መደረሱ የውጭ ምንዛሪን ለማዳን የሚኖረው ፋይዳም የላቀ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት በርካታ ሥራዎችን በትብብር በመስራት መልካም ግንኙነት መመስረታቸውን ተናግረዋል፡፡

ኤሌክትሪክ ለሀገር ኢኮኖሚ ወሳኝና መተኪያ የሌለው ሞተር ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተቋማቸው በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ ተቋም በማድረግ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት እንዲኖረው በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ስምምነት የተፈረመበትን የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒግ (ኢ.አር.ፒ) መሰረተ ልማት ዝርጋታና አቅም ግንባታ ስራ በተያዘለት በጀትና ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ተወልደ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ተቋም መሆን እንዲችል ተቋማቸው ከተለያዩ ሃገራት የቀሰመውን ልምድና ተሞክሮ በማጋራት የአሰራር ሥርዓቶቹን ለማዘመን ተቋማቸው ጥረት ያደርጋል፡፡

ፕሮጀክቱ በሃያ ሁለት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሙሉ ትግበራ የሚገባ ሲሆን አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪውም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸፈን ከ143 ነጥብ 7 ሚሊዬን ብር በላይ ነው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

5 × 1 =