የኢትዮ – ኬንያ የኢነርጂ ሚኒስትሮች የሁለትዮሽ ውይይት ተካሄደ

Published by corporate communication on

የኢትዮ – ኬንያ የኢነርጂ ሚኒስትሮች የሁለትዮሽ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የኢፌዲሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ እና የኬንያ ኢነርጂና ነዳጅ ሚኒስትር ሚስተር ቻርለስ ኬተር ከልዑካን ቡድኖቻቸው ጋር በመሆን ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትሮቹ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት ሁለቱ ሀገራት ለኃይል መሰረተ ልማት ዝርጋታ ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ አፍሰዋል።

ከ አንድ ሺህ በላይ ኪሎ ሜትሮች የሚረዝመው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሊያስተሳስር የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት በመሆኑ መጠናቀቁ ለሁለቱ ሀገራት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ሚኒስትሮቹ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በኩል የተዘረጋው የ412 ኪሎ ሜትር የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመርና የዲሲ ኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ የሙከራና ፍተሻ ስራ የተከናወነ ሲሆን በኬንያ በኩል መዘርጋት ካለበት 633 ኪሎ ሜትር ውስጥ 30 ኪሎ ሜትር ብቻ መቅረቱ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል።

በመሆኑም ቀሪ ስራውን በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኬንያ ኢነርጂና ነዳጅ ሚኒስትር ቻርለስ ኬተር አስታውቀዋል።

ዛሬ የተጀመረው የሁለትዮሽ ውይይት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ሲጠናቀቅ የሙከራ ስራ በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ ለመምከርና ቀደም ሲል የተፈረመው የኃይል ሽያጭ ስምምነት ላይ ያልተጠናቀቁ ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ ነው።

ስምምነቱንም በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ እንዲያጠናቅቁ ሚኒስትሮቹ ለባለሙያዎች ቡድን አቅጣጫ ሰጥተዋል።

የሁለቱ ሀገራት የባለሙያዎች ቡድን ዝርዝር በሆኑ የስምምነትና የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ለቀጣዮ ሶስት ቀናት የሚመክሩ ይሆናል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

three + 2 =