የኢትዮ-ኬንያ የኃይል ሽያጭ ስምምነት ተጠናቀቀ

Published by corporate communication on

ለዓመታት ድርድር ሲደረግበት የቆየው የኢትዮ- ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ድርድር ትናንት ማምሻውን በስምምነት ተጠናቋል፡፡

ስምምነቱን የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በተገኙበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኬንያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢንጂነር ጎፌሪ ሙሊ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ኢትዮጵያ አሁን ላይ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ለመሸጥ የሚያስችላት ሲሆን በቀጣይ ደግሞ ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን እስከ 400 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እያካሔደች የምትገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት በሀገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ከማድረጉም ባሻገር ፋይዳው የጎላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሱዳን እና ጅቡቲ ጋር የኃይል ሽያጭ እያካሄደች ሲሆን ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ስምምነት ፈርማለች፡፡

የግንባታ ሥራው በ2008 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ከ183 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ መጠናቀቁን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

two × 5 =